
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመከተል ወደ ተሀድሶ ስልጠና እንዲቀላቀሉ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው፥ መንግስት በክልሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን ቢቆይም፥ የሕወሓት ቡድን በፕሪቶሪያው ስምምንት የፈረመውን ትጥቅ የማስፈታት ስምምነት በማፍረስ ወደ ተሃድሶ ማዕከል ለመግባት ፈቃደኛ የነበሩ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና እንዳይወስዱ እያደናቀፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ጦርነቱ እጅግ የከፋ የጦርነት አካሄድ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፥ ቡድኑ ወጣቶችን አስገድዶ በማፈስ ለጦርነትና ለከፋ እልቂት እየዳረገ ይገኛል ብለዋል።
የትግራይ ወጣት እራሱን ከጦርነት ለማትረፍና ወደ ተሀድሶ ማዕከል ለመቀላቀል እየጣረ ቢሆንም በጽንፈኛው የህውሀት ቡድን ተባብሶ የቀጠለው የጦርነት መንገድ ፈተና ውስጥ እንደከተተው ገልጸዋል።
በክልሉ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት በማስረከብ ወደ ተሃድሶ ማዕከል እንዲገቡ ሲሉም ምክትል ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስትን የሰላም ጥሪን ተቀብለው ለሚመጡ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ መደበኛ ሕይወት ለማስገባት አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።
ሰላም ፈላጊ ለሆኑ ታጣቂዎች በማይጨውና መሆኒ ከተሞች፣ በመቀሌ፥ በአክሱም ፥ በሽሬ፣ አዲግራትና በውቅሮ ከተሞች የቅበላ ማዕከላት መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።
በ-ሰላማዊት ወንድወሰን












