
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያደረገ ይገኛል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ሀይሉ፣የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጨምሮ የክልል አመራሮች እና የጸጥታ አካላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ሀይሉ፥ የ2018 ዓ.ም 7ተኛ ጠቅላላ ምርጫን ፍትሀዊ እና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፥ የዚሁ አካል የሆነና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ማድረግ አስፈልጓል ብለዋል።
ቦርዱ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነበሩ ክፍተቶች እንዳይደገሙ እና የነበሩ በጎ ተሞክሮዎችን ለማስቀጠል ሰፊ ውይይት ሲያደርግ መቆየቱንም ያስታወሱ ሲሆን፥ የዘንድሮው ምርጫም ስኬታማ እንዲሆን በየክልሉ ያለውን የሰላምና ጸጥታ ሁኔታን የመፈተሽ ስራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ምርጫ ቦርድ በየክልሎች ያለው የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ መረጃዎችን መሰብሰቡን ጠቅሰው፥ ዛሬ የተጀመረው ምክክርም ውጤታማ ምርጫ እንዲደረግ ቀድመው ሊሰሩ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ለመወያየትና ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል ነው ብለዋል።
7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ፍትሀዊና ገለልተኛ እንዲሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብን ይጠይቃል ያሉት ሜላተ ወርቅ፥ ለዚህም በሀላፊነት በጋራ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲካሄድ የጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱ ይታወሳል።
በ-ሰላማዊት ወንድወሰን












