
ስምምነቱን አስመልክቶ በተካሄደው መድረክ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አመራሮች ፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች እንዲሁም በመንግስት የቀረበውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የአፋህድ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በስምምነቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ በክልልሉ የነበረው ግጭት ከፍተኛ ውድመትን ያስከተለ ነው፤ ይህም ህዝባችን ሊያገኝ የሚገባውን የሰላምና የልማት ያሉ ሰብአዊ መብቶችን አሳጥቷል ብለዋል።
በዚህ በሰለጠነ ዘመን ከሰላም ይልቅ አፈ ሙዝ ይዞ መፉተግ ጊዜውን የማይመጥንና በትውልድ ተወቃሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ዛሬ ላይ ሰላምን መርጠው ወደ ሰላም መንገድ የመጡት የአፋህድ አመራሮች ተገቢውንና ለትውልድ የሚበጅ ውሳኔ በመምረጣቸው ምስጋና አቅርበዋል።
ሌሎች ቀሪ ሀይሎችም የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፋህድ ከፍተኛ አመራር ኮለኔል ፈንታው ሙሀባ በበኩላቸው ስምምነቱን ባለፉት ጊዜያት በአፍሪካ ህብረትና በኢጋድ አማካኝነት በህጋዊ መንገድ ስንወያይ ቆይተናል ብለዋል።
ስምምነቱ ያለፈውን የሚያጠናክርና ህጋዊ በሆነ መልኩ የተፈፀመ መሆኑን ገለጸዋል።
ባለፈው ጦርነት የአማራ ህዝብ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የአይን እማኝ ነን ክልሉም ከዚህ በላይ ጦርነት የመሸከም አቅም የለውም ብለዋል።
ጦረነቱ በጥቅሉ በህወሃትና ሻዕቢያና በግብፅ መጠለፉን ያነሱት ኮለኔሉ የህዝብን ጥያቄ ከአጥፊ ሀይሎች ጋር በማበር አይመለስም ነው ያሉት።
በዚህም የሰላም አማራጭን ወስደናል ሌሎች ቀሪ ሀይሎችም የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀበሉ ብለዋል።
ባለፈው ህዳር 25 2018 ዓ.ም የአፋህድ ከፍተኛ አመራር ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ጋር በአፍሪካ ህብረትና በኢጋድ አደራዳሪነት የዘላቂ ሰላም ማፅኛ ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል።
አመራሮቹ በወቅቱ ለቀሪ ሀይሎች ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ባለፋት ጊዜያት በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪን ተቀብለው በመግባት ላይ ይገኛሉ።
በ-የአብስራ ሚሊዮን












