December 16, 2025
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢቢሲ ፈፅሞብኛል ላሉት የስም ማጥፋት ወንጀል የ10 ቢሊየን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ጠየቁ፡፡

ትራምፕ ባቀረቡት ባለ 33 ገፅ ክስ ፤ ቢቢሲ ስሜን በውሸት በማጉደፍ፣ ሀሰተኛ እና ንቀት ቀስቃሽ ምስል በማሰራጨት በ2024ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ጣልቃ ለመግባት እና ተጽዕኖ ለማሳደር አግባብነት የሌለው ሙከራ አድርጓል ሲሉ ከሰዋል። በዚህም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢቢሲ ላደረገው የስም ማጥፋት እና አሉታዊ ተግባር የ10 ቢሊየን ዶላር ካሳ ሊከፍል ይገባል ሲሉ ክስ መስርተዋል፡፡

ክሱ የቀረበው ቢቢሲ በጥር 6፣ 2021 ከተሰማው የፕሬዝደንት ትራምፕ ንግግር ላይ የተቀነጫጨቡ ክፍሎችን አጣምሮ በመጠቀም አሳሳች ዘገባ አቅርቧል በሚል ነው። ቢቢሲ ንግግራቸውን ቆርጦ ያቀረበበትን መንገድ በተመለከተ ይቅርታ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፤ትራምፕ ይቅርታ ብቻ በቂ አይደለም በማለት ክስ እንደሚመሰርቱ ዝተው ነበር፡፡
ባሳለፍነው ሳምንትም ትራምፕ በፕሬዝዳንታዊው አውሮፕላን ‘ኤር ፎርስ ዋን’ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ በሚቀጥለው ሳምንት ከ1 እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ክስ እንመሰርታለው ብለው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በ-ሰላማዊት ወንድወሰን












