የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እና ሲዳማ ባንክ የክፍያ አጋርነት ስምምነት አደረጉ።
በዚህም ከምርት ገበያው ጋር የክፍያ አጋርነት ስምምነትን በማድረግ ሲዳማ ባንክ 26ኛ ባንክ መሆኑ ተገልፅዋል። ስምምነቱን የምርት ገበያው ዋና ስራ አስፈፃሚ መርጋ ባይሳና የሲዳማ ባንክ ፕሬዝዳንት ታደሰ አጢሃ ተፈራርመዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ምርት ገበያው ተገልጋዮች ክፍያቸውን ባሻቸው ባንክ እንዲፈፅሙ ለማስቻል የሲዳማ ባንክን ከክፍያ አጋራችን አንዱ አድርገናል ብለዋል።
ምርት ገበያው በ2017 በጀት አመት ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶች በኦንላይን ግብይት መፈፀሙን ተናግረዋል። ለአርሶ አደሮች በምርት ማስያዣነት ብቻ 1.1 ቢሊዮን ብር ብድር እንዲመቻች መደረጉንም ጠቁመዋል።
የሲዳማ ባንክ ፕሬዝዳንት ታደሰ አጢሃ የምርት ገበያውን አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች በስምምነቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀው፤ ሌሎችም የምርት ገበያው ተገልጋዮች እንዲቀላቀሏቸው ጠይቀዋል።
ምርት ገበያው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በመላ ሀገሪቱ ባሉት 26 ቅርንጫፎቹ በአማራጭነት አገልግሎቱን እየሰጠ መሆኑን ጠቁሟል።
በ- አብርሃም በለጠ












