ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ተጫዋቾቹ የእረፍት ሰዓት ቃለ መጠይቅ እንዲያደርጉ አይፈቅዱም ነበር ሲል ዋይኒ ሩኒ ተናገረ።
The Wayne Rooney Show በሚል ቢቢሲ ላይ አዲስ ፖድካስት የጀመረው የቀድሞ የማንችስተር ዩናይትድ ኮኮብ ዋይኒ ማርክ ሩኒ ተጨዋቾች በእረፍት ሰዓት ከሚደረግ ቃለ መጠየቅ ምን አይነት ጥቅም እንደሚያገኙ አይገባኝም ሲል ተደምጧል።
ሩኒ በማንቸስተር ዩናይትድ ለዘጠኝ አመታት አለቃው የነበሩት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ሃሳቡ በአሰልጣኝነታቸው ጊዜ ቢነሳ በፅኑ ይቃወሙት ነበር ብሎ ያምናል። በእርግጥ ስኮትላንዳዊው አሠልጣኝ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች አጋማሽ ላይ ቃለ መጠይቅ ሰጥተው ያውቃሉ።
ግን ይላል ሩኒ “ሰር አሌክስ በምን መንገድ ምላሽ እንደሚሰጡበት አውቃለው፤ በጥሩ መልኩ እንደማይሆንም እርግጠኛ ነኝ” ሲል ሀሳቡን ይገልፃል።
የቀያይ ሰይጣኖቹ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አክሎም “ወደ ዲሲ ዩናይትድ ስሄድ በእረፍት ሰዓት ቃል መጠይቅ እንድሰጥ ደጋግመው ይጠይቁኝ ነበር እኔ ግን አልተቀበልኳቸውም። የተጨዋቾች ትኩረት እና አስተሳሰብ በጨዋታው ላይ እና በሚቀጥሉት 45 ደቂቃዎች ምን መሆን እንዳለበት እንዲሁም እንዴት የተሻለ መስራት እንዳለበት ማሰብ ላይ ብቻ ሊሆን ይገባል” በማለት ሀሳቡን ቋጭቷል።
የአርሰናሉ አምበል ማርቲን ኦዴጋርድ ባለፈው ሳምንት ክለቡ አርሰናል ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ባደረገው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አጋማሽ ላክ ከስካይ ስፖርትስ ጋር ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ ተስተውሏል።
በ- ዳንኤል መምሩ












