በአይነቱ የመጀመሪያ ነው የተባለለት ዓለም አቀፍ የቴምር ፌስቲቫል በአፋር ክልል ሰመራ ከነሃሴ 20 እስከ 22 የግብርና ሚኒስቴር ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጋር በመተባባር እንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡
ፌስቲቫሉን የግብርና ሚኒስቴር፣ የአፋር ክልል እና መቀመጫውን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደረገው ‘ካሊፋ ኢንተርናሽናል አዋርድ ፎር ዴት ፓልም ኤንድ አግሪካልቸር ኢኖቬሽን’ በጋራ እንዳዘጋጁት ተገልጿል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ፌስቲቫሉን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በቴምር ልማት መስክ ያላትን እምቅ አቅም ለማሳየት ያስችላል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል በምታደርገው ጥረት ቴምር አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው በፌስቲቫሉ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የቴምር ዝርያዎችን የሚያሳይ ኤግዚቢሽን፣ ሳይንሳዊ ሲምፖዚየም፣ የቴምር እርሻዎችን ጎብኘት እና የባለድርሻ አካላትን የልምድ ልውውጥ ያካትታሉ።
የቴምር አምራቾች ለሚገጥማቸው ችግር መፍትሄ ማፈላለግ፣ በተለያዩ አገራት አምራቾች መካከል ግንኙነት መፍጠርና የገበያ ትስስር እንዲጠናከር እንደሚያስችል ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
የአፋር ክልል የግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ያሲን አሊ በክልሉ ፌስቲቫሉን ለማስተናገድ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ የክልል ተሳታፊዎችና ከአስር ሀገራት የተውጣጡ 40 አለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ አጋሮች እንደሚሳተፉ ይጠበቃልም ተብሏል፡፡
በ ማህሌት ግርማ












