ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከአስደናቂው የአንደኛ ሳምንት ቆይታው መልስ ዛሬ ምሽት 4:00 ዌስትሃም ዩናይትድን እና ቼልሲን በሚያገናኝ ጨዋታ ይመለሳል።
ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አዳጊው ሰንደርላንድ የሶስት ለዜሮ ያልተጠበቀ ሽንፈት የቀመሱት ግርሃም ፖተር፤ መዶሻዎቹን ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ የወረዱትን የሊጉን ክለቦች ከንፅፅር የምናወጣ ከሆነ በሞከሩዋቸው ሙከራዎች፣ ኢላማቸውን በጠበቁ ሙከራዎች፣ ከክፍት ጨዋታ ከፈጠሩዋቸው እድሎች እና ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ባቀበሉዋቸው የኳስ ቁጥሮች የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይቀመጣሉ። ይህም አሰልጣኙ ላይ ገና ከወዲሁ ጫናዎች እንዲበረክቱ እያደረገ ይገኛል።
ባሳለፍነው ሳምንት ከክርስትያል ፓላስ ጋር 0 ለ 0 የተለያዩት ሰማያዊዎቹ ባንፃሩ በሳምንቱ በሊጉ ከየትኛውም ክለብ በላይ የሚያደርጋቸውን 72 በመቶ የኳስ ቁጥጥር ይዘው ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ቢሆንም ከ568 የኳስ ቅብብላቸው ግን አንድም ነፍስ ያለው ወደ ግብ የተቀየረ ኳስ አለመታየቱ የሚዘነጋ አይደለም።
በጨዋታው ዌስትሃሞች የሰመርቪሌን ግልጋሎት የማያገኙ ሲሆን ቼልሲዎች በበኩላቸው ሌቪ ኮልዊል፣ ቤኖይት ባድያሺሌን እና ቶሲን አደራቢዮን የማያገኙ ይሆናል። ባለፈው ሳምንት ጥሩ አቋም ያሳየው ጆሽ አቺምፖንግ በአንፃሩ ይህንንም ጨዋታ ዳግም በቋሚነት እንደሚጀምር ይገመታል።
ቅዳሜ ቀን 8:30 በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ ከ ቶተንሃም የሚገናኙ ይሆናል።
በአንጅ ፖስቼግሉ ስር ቀጥተኛ እና ፈጣን ጨዋታን ያስመለከተን የሰሜን ለንደኑ ክለብ በአዲሱ አሰልጣኝ ቶማስ ፍራንክ ስር ደግሞ ከቆሙ ኳሶች አደገኛ ቡድን ሆኖ እንደሚመጣ ፍንጭ ሰጥቷል። ለአብነት ያህል እንኳን ማይኪ ቫንዴቬን በቶማስ ፍራንክ ስር በቋሚነት ከጀመረባቸው ሁለት ጨዋታዎች PSG ላይ ግብ ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው።
ማንቸስተር ሲቲዎች በበኩላቸው አዲሱ ፈራሚያቸው ቲያኒ ሬይንደርስ ድንቅ አቋም ባሳየበት ጨዋታ 4 ግቦችን አስቆጥረው ማሸነፋቸው የሚታወስ ሲሆን የነገው የኢትሃድ ጨዋታም በጉጉት የሚጠበቅ ነው። ቅዳሜ አምሻሽ 11 ሰዓት ላይ ሶስት ጨዋታዎች የሚስተናገዱ ይሆናል።
አሰልጣኛቸውን ጨምሮ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በክረምቱ የተነጠቁት ብሬንትፎርዶች በመክፈቻው ጨዋታ በኖቲንግሃም ከደረሰባቸው ሽንፈት ቡኃላ የአሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬን አስቶንቪላ ይገጥማሉ።
ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በሊጉ ግብ ያልተቆጠረበት ጨዋታ ለመመልከት ለ4 ሳምንታት ለመጠበቅ የተገደድን ሲሆን በዚህ አመት ግን ገና በመጀመሪያው ሳምንት 2 የዜሮ ለዜሮ መርሃግብሮችን መታዘብ ችለናል። ከነዛ ሁለት ጨዋታዎች አንዱ ኒውካስትል እና ቪላን ነጥብ ያጋራው ጨዋታ መሆኑ አይዘነጋም። ታድያ ይህ የብሬንትፎርድ እና የአስቶንቪላ ጨዋታ የመጀመሪያ የሊግ ሶስት ነጥባቸውን ለማግኘት የሚያደርጉት ትንቅንቅ ይሆናል።
በሌላ ጨዋታ ወልቭስ እና በርንማውዝ ሲገናኙ፤ የአሰልጣኝ ቪቶር ፔሬይራ ወልቭስ የቱንም ያህል ጫና ውስጥ ቢሆን ኳስን ይዞ ለመጫወት የሚሞክርበት መንገድ አንዶኒ ኢራዮላ ይዞት የሚመጣውን የፕሪሲንግ ጫና እንዴት ሊቋቋም ይችላል የሚለውን ለማየት አጓጊ ያደርገዋል።
በርንማውዞች ልክ እንደ ብሬንትፎርድ ሁሉ ወሳኝ ተጫዋቾችን ቢሸጡም ባሳለፍነው ሳምንት አንፊልድ ላይ ተሸንፈውም እንኳ ያሳዩት አቋም በዚህ አመትም ብዙ ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጠ ነው።
ፕሪምየር ሊጉ አሁን ላይ ከፍ ያለ ፍጥነት፣ ጉልበት፣ ቀጥተኝነት እና ከኳስ ውጪ ያለ መታተርን የሚፈልግ ሊግ ሆኗል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ቁጥር ተከታዩ ነው። በ2018/19፤ 389 ፈጣን መልሶ ማጥቃትን ያስተናገደው ሊግ በተጠናቀቀው የውድድር አመት ይህን ቁጥር በእጥፍ አሳድጎ 775 ፈጣን መልሶ ማጥቃቶች ተስተናግደውበታል።
ታድያ በርንሌይ እና ሰንደርላንድ የሚገናኙበት የነገ ጨዋታም እንዲህ ያለውን የጨዋታ ባህሪ በጉለህ ሊያሳይ እንደሚችል ይጠበቃል። አዲስ አዳጊዎቹ ሰንደርላንዶች ምልመላቸው ለዚህ የፈጣን መልሶ ማጥቃት ጨዋታ የሚሆን እንደሆነ ከዝውውራቸው መረዳት ይቻላል። የዌስትሃሙ ድላቸውም የጨዋታ መንገዳቸውን ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው።
በቅዳሜ የመጨረሻ ጨዋታ ምሽት 1:30 ላይ መድፈኞቹ ሊድስ ዩናይትድን ያስተናግዳሉ። የመጀመሪያ ፈተናቸውን በእጅጉ ተቸግረውም ቢሆን በድል ያጠናቀቁት አርሰናሎች፣ የኤዜን ዝውውር ዜና ከሰሙ ቡኃላ የሚያደርጉት ጨዋታ ይሆናል።
መድፈኞቹ ምንም እንኳን ማንቸስተር ዩናይትድን ያሸነፉበት የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ በሊጉ ድልን ያሳኩበት ሶስተኛ ተከታታይ ጨዋታ ቢሆንም በሁለት ግብ ልዩነት ካሸነፉ ግን ስድስት ወራት መቆጠራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በጨዋታው ማሸነፍ የሚችል ከሆነ በ43 ተከታታይ ጨዋታዎች ሜዳቸው ላይ አዲስ አዳጊ ክለቦችን ማሸነፍ በመቻል ከ2001 -2015 ድረስ ባለው ጊዜ በቼልሲ የተያዘውን ሪከርድ መጋራት የሚችሉ ይሆናል።
ሊጉ እሁድም በሶስት መርሃግብሮች ሲቀጥል 10 ሰዓት ላይ ክርስትያል ፓላስ ከኖቲንግሃም ፎረስት እንደዚሁም ኤቨርተን ከብራይተን የሚጫወቱ ይሆናል። በእለቱ ምሽት 12:30 ላይ በሚካሄድ ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ፉልሃም ይገናኛሉ።
የማርኮ ሲልቫ ቡድን ባለፈው አመት ከሊጉ ወገብ በላይ ካጠናቀቁ ቡድኖች ጋር ባደረገው ጨዋታ ማሳካት ከነበረበት 54 ነጥብ 30 ነጥቦችን ማሳካት ሲችል ዘንድሮም ከፍ ያለ የመገዳደር አቅምን ፈጥሮ እንደሚመጣ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በበኩለቸው በቡድናቸው ላይ ከፍ ያለ ፈጠራ እና ታታሪነትን ጨምረው መምጣታቸውን ያስመሰከሩ ቢሆንም መሃል ሜዳቸው ላይ ያለውን ክፍተት መድፈን አለመቻለቸው ትልቁ ጉድለታቸው መሆኑ እየተጠቆመ ይገኛል።
የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሰኞ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ከሜዳ ውጪ ከፍ ያለ ፍልምያ ውስጥ የገቡትን ኒውካስትል ዩናይትድን ከ ሊቨርፑል ጋር ዳግም በሜዳ ላይ የሚያፋልም ይሆናል።
ቀያዮቹ ባለፈው ሳምንት በርንማውዝን ማሸነፍ ቢችሉም በጨዋታው የተጋለጡባቸው አምስት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ግን ባለፈው አመት አንፊልድ ላይ በየትኛውም ጨዋታ ከተፈጠሩባቸው የመልሶ ማጥቃት እድሎች ሁሉ የበለጠ ነው።
ይህንንም ተከትሎ በአንቶኒ ኢላንጋ፣ አንቶኒ ጎርደን እና ሃርቬይ ባርንስ የሚመራው የኒውካስትል ዩናይትድ የፊት መስመር በመልሶ ማጥቃት ሊቨርፑልን ጫና ውስጥ ሊከት እንደሚችል በርካታ የእግርኳስ ተንታኞች ግምታቸውን እያስቀመጡ ነው።
የአሌክሳንደር ኢሳክ ጉዳይም ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕስ ሲሆን የኒውካስትል ደጋፊዎች በጨዋታው ሊቨርፑላውያኑ ላይ ከፍ ያለ የተቃውሞ ድምፅ ሊያሰሙ እንደሚችሉ ተዘግቧል።












