ከምዕተ ዓመታት በፊት ለብዙ አፍሪካውያን የባቡር አገልግሎትን ያስተዋወቀው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር በኋላም የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎት ለረጅም ዓመታት ግዙፍ ሀብቱን ይዞ ተቀብሮ የቆየ ተቋም ነበር።

ሀገራችን ቀድማ ጀምራ ኋላ የቀረችው መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር አፍርሰው የመጀመር የመጥፎ ልማድ እስረኛ ሆና ለመቆየቷ አንዱ ማስረጃ ነው።
የለውጡ መንግሥት በተከተለው አዲስ ዕይታና በወሰደው እርምጃ መሠረት የሀገር አንጡራ ሀብት የሆነው ተቋም፣ ባቡር እና የባቡር መሰረተ ልማት ከተቀበረበት ጣሻ ውስጥ ተፈንቅሎ እየወጣ ለመሆኑ በግቢው የሚታዩ ነገሮች ሁሉ በገፅታቸው ይናገራሉ።
የተደበቀው ሀብታችንን የመግለጥና የትናንት ወረትን ለሀገራዊ ብልፅግና የመጠቀም መርህን በማንገብ በተጀመሩ ሥራዎች የትራንስፖርት፣ የወርክሾፕና የጥገና ሥራዎች በለውጥ ሀዲድ ላይ ናቸው።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስር ያለው የድሬዳዋ ደወሌ ባቡር አገልግሎት የተበተነውን ሠራተኛ በመሰብሰብ የቆሙ ባቡሮችን ጠግኖ ወደ ሥራ በማስገባት አሁን ላይ በሳምንት ሁለት ቀን አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ለትራንስፖርት ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችን አገናኝቷል።
በመጭው አመትም አገልግሎቱን ከሁለት ቀናት ከፍ ለማድረግ ዐቅዶ እየሰራ ነው። ለስኬቱ የፌደራል መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል።
በሁሉም መስክ ራሳችንን ለመቻል የጀመርነውን ጉዞ ለማሳካት ከፍተኛ አቅም አለን። በባቡር አገልግሎት ቀድመን ጀምረን ወደኋላ መቅረታችን ቢያስቆጭም ከራሳችን አልፎ አፍሪካን በባቡር ለማስተሳሰር በአዲስ ምዕራፍ በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል።












