የጃፓን ካራቴ ሾቶ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ካሬቴ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ውድድር ማዘጋጀቱን አስታውቋል።
ውድድሩ ከፊታችን ባለው ከነሐሴ 16-18 የሚደረግ ሲሆን ከ300 በላይ ተወዳዳሪዎች በኦንላይን ተመዝግበው ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል። የጃፓን ካራቴ ሶቶ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ ከተመሰረተ 7 አመት ያስቆጠረና በአጭር ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ እና የክልል ከተሞች ውጤታማ የካራቴ ክለቦችን መፍጠሩ ተመላክቷል።
የJKS ፕሬዚዳንት ሰለሞን ዘውዱ፤ በሁለቱም ፆታ ከልጅ እስከ አዋቂ ተሳትፎ የሚያደርግበት ውድድር መሆኑን አንስተዋል። በውድድሩ ላይ አካል ጉዳተኞችም ተሳትፎ እንደሚያደርጉ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ ለአሸናፊዎች አጓጊ ሽልማት ተዘጋጅቷል።
የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሙሉነት ጎሳዬ፤ Jks በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዘርፉ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል። ለውድድሩ ከክልል ለሚመጡ ስፖርተኞች አመቺ የማረፊያ ስፍራ መዘጋጀቱ በመግለጫው ተነግሯል።
ከዚህ ቀደም በተዘጋጁት ውድድሮች ኢትዮጵያን በአለም መድረክ ያስጠሩ አትሌቶች እንደመገኘታቸው በዘንድሮውም በተመሳሳይ ብቁ ስፖርተኞች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












