አብርሀም በለጠ
ከነሐሴ 26 እስከ 30 የሚድሮክ ሳምንት አውደ ርዕይ “ሚድሮክ ለሀገር” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ ተመላከተ። ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለፋት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የተቋሙ ኮሚኒኬሽንና ፕሮሞሽን ኃላፊ ሁናቸው ታዬ አመላክተዋል።

ተቋሙ ከገቢው 10 በመቶ ያክሉን ለማህበረሰብ አገልግሎት እያዋለ መሆኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል። ከነሐሴ 26 ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በሚካሄደው አውደ ርዕይ የሚድሮክ ምርቶችና አገልግሎቶች በሚሊኒየም አዳራሽ ለዕይታ እንደሚቀርቡ ተመላክቷል።
በፓናል ውይይቶችም፣ ባለሙያዎች የሚድሮክና የሌሎች የግል ዘርፉ ተቋማት ለሀገር የሚኖራቸው ሚና ምክክር እንደሚደረግበት ተጠቁሟል። በአውደ ርዕዩ ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፋ ይጠበቃል። ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።












