የቀድሞ ውድድር ዘመን የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ለወትሮው ክለቦች የሚያስፈርሟቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች ከነባር የቡድን ስብስባቸው ጋር የሚያዋህዱበት የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ከአካዳሚ የሚገኙ ወጣት ተጫዋቾች ደምቀው የሚታዩበት ወቅት እየሆነ መጥቷል።
የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ማክስ ዶውማን እና ሳልመንን የመሳሰሉ የመጪው ዘመን ኮከቦችን ባስመለከተን ተመሳሳይ ጊዜ፤ የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑልም የወደፊቱ ጊዜ እንቁዎችን ለእግር ኳስ አፍቃሪያን አሳይቷል።
ሊቨርፑል በዝውውር ገበያው ከ263 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ወጪ በማድረግ ፍሎሪያን ቪትዝ፣ ሁጎ ኤኪቲኬ፣ ጀረሚ ፍሪምፖንግ እና ሚሎስ ኬርኬዝን የግሉ ማድረግ ችሏል። በቡድን ስብስባቸው በርካታ ታዳጊዎችን የያዙት አሰልጣኝ አርነ ስሎት በአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ላይ ረጅም ደቂቃ የመጫወት ዕድል ሲሰጧቸው እየተስተዋለ ይገኛል።
ትላንት ከስፔኑ አትሌቲክ ቢልባኦ ጋር በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት ጊዜ የተጫወቱት ቀዮቹ በሁለቱም ወቅት ድል ማድረግ ችለዋል።
በመጀመሪያው ጨዋታ ኮከብ የነበረው የ 16 አመቱ አጥቂ ሪዮ ንግሞሃ በእስከሁኑ በሜዳ ላይ የሚያሳየው እንቅስቃሴው የቅድመ ውድድር ዘመን የሊቨርፑል ክስተት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ለእንግሊዝ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሚጫወተው ንግሞሃ በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ብቻ አንድ ጎል አስቆጥሮ፣ አንድ ደግሞ ወደ ግብ የተለወጠ ኳስ ማቀበሉ ሙገሳ እንዲቸረው አስችሏል።
በድጋፍ ባህላቸው የሚታወቁት የቀዮቹ ደጋፊዎች ከአሁኑ ህብረዝማሬ ያወጡለት ታዳጊ ባሳየው አስደናቂ አቋም መነሻነት በኮከቦች በተሞላው የአርናስሎት ስብስብ ውስጥ የመጀመሪያው ቡድን አባል ለመሆን በቅቷል።
የቀዮቹ ታሪካዊ ተጫዋቾች፣ ሊቨርፑል ለአመታት ከስቴቨን ጄራርድ እስከ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ታዳጊ ቡድኑ እንዳፈራው ሁሉ ቀጣዩ ባለተራ ንግሞሃ ይሆናል በሚል አስተያየታቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ተጫዋቹን በታዳጊ ቡድን ያሰለጠኑት አሰልጣኞችም አስተያየት ይህንኑ የሚጋራ ይመስላል። ንግሞሃ ከኳስ ጋር ያለው ቅልጥፍና፣የሚያሳየው ድፍረት እና ብስለት፣በሁለቱም እግሮቹ የመጫወት ክህሎት መያዙ ተደናቂነት እያፈራለት ይገኛል።
ንግሞሃ በሊቨርፑል የመጀመሪያ የመሰለፍ ዕድል የተሰጠው በጥር ወር በኤፍ ኤካፕ ከአክሪንግተን ጋር በነበረ ጨዋታ ሲሆን፣በ16 አመት ከ135 ቀን በጨዋታው በቋሚነት በመሰለፍ በክለቡ ታሪክ ወጣቱ ተጫዋች ሆኗል።
ተጫዋቹ ከሚያሳየው አስደናቂ ብቃት በተጨማሪ የመጀመሪያ ቡድን አባል እንዲሆን ካስቻሉ ምክንያቶች ውስጥ እርሱ በሚሰለፍበት ስፍራ የሚጫወተው ዲዮጎ ጆታ በድንገት ማለፉ፤ የልዊስ ዲያዝ ወደ ባየርን ሙኒክ መጓዝ እና ዳርዊን ኑኔዝም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናል መባል ለታዳጊው ተጫዋች የመጫወቻ ደቂቃ ለማግኘት መልካም አጋጣሚ መፍጠሩ ተገልጿል።
ሊቨርፑል የኒውካስትል ዩናይትዱን አጥቂ አሌክሳንደር ኢሳቅን ለማዘዋወር እያደረገ ያለው ሙከራ አለመሳካቱም ተጫዋቹ በአዲሱ የውድድር አመት በርካታ ዕድሎችን እንደሚያገኝ አመላካች ነው ተብሏል።
ዋይን ማርክ ሩኒ በ16 አመት ዕድሜው አርሰናል ላይ ባስቆጠራት ግብ “ስሙን እንዳትረሱት በሚል”እንግሊዝ አዲስ ኮከብ ተወለደላት እንደተባለው፤ ንግሞሃም ይህው ተመሳሳይ ትንቢት እየተነገረለት ይገኛል።
በእርግጥ ተጫዋቹ አሁንም ድረስ በሚሰጣቸው አስተያየቶች እንደማይቸኩል እና ብዙ መማር ይጠበቅብኛል ማለቱ፤ ተጫዋቹ ታይቶ እንዳይጠፋ ለሰጉ ሰዎች ጥሩ መልዕክት ሆኗል። ሻምፒዮኑ ሊቨርፑል በተከታታይ አመት የሊጉን ክብር ለማሳካት በሚያደርገው ጉዞ ንግሞሃ የት ይደርሳል የሚለውን ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












