ኢትዮጵያ ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ቱሪስቶች በቅርበቷም ሆነ በአየር ንብረቷ የተሻለ ተመራጭ ሀገር የመሆን አቅሟን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገነባች በምትገኛቸው የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች እያሳየች ትገኛለች፡፡
የምስራቁን የኢትዮጵያ ክፍል፤ የአፍሪካ ብሎም የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የሚገኙ ቱሪስቶች ያማረ እና ምቹ የእረፍት ጊዜ ሊያሳልፉ የሚችሉበት ሪዞርትም ሶማሌ ክልል እየተገነባ ይገኛል፡፡
ከጅጅጋ ከተማ በ28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የሸበሌ ሪዞርት 380 ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን በርካታ ቱሪስቶችን ማስተናገድ የሚችሉ ዘመናዊ፣ ምቹ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ አገልግሎቶችን የያዙ 8 መንደሮች አሉት፡፡
ጅግጅጋ ከተማን እና አካባቢዋን ወደ ታላቅ የቱሪዝም መዳረሻነት የመለወጥ አቅም እንዳለው የታመነበት የሸበሌ ሪዞርት ግንባታው ከተጀመረ አንድ አመት ተኩል ሆኖታል፡፡ በተለይም ግንባታው የክልልን ባህል እና እሴትን በሚያንጸባርቁ የኪነ ህንጻ ጥበብ የተዋቀሩ ናቸው፡፡
በፌደራል መንግስት እና በክልሉ በጀት እየተገነባ የሚገኘው ሪዞርቱ በ1.92 ቢሊየን ብር ፈሰስ ተደርጎበታል፡፡ የመብራት ውሃ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በሪዙርቱ የተሟላ ሰሆን 13.5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ተካሂዷል፡፡
ሪዞርቱ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን፣ ሆቴሎችን፣ መናፈሻዎችን፣ የስብሰባ አዳራሾችን እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ያካተተ ነው።
ዘመኑን እና የአከባቢውን ባህል በዋጀ ኪነ ህንጻ የተገነባው የሸበሌ ሪዞርት ለአፍሪካ ብሎም ከመካከለኛው ምስራቅ የሚመጡ ቱሪስቶች ምቹ ማረፊያ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡












