ስካይ ጀርመን እና ኪከርን የመሳሰሉ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ሊቨርኩሰን በቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ እና አያክስ አሰልጣኝ ላይ ጠንካራ ፍላጎት አለው።
አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ካርሎ አንቼሎቲን በመተካት የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ መሆኑ አይቀሬ እየመሰለ መጥቷል።
ሊቨርኩሰኖች ስፔናዊውን አሰልጣኝ ለመተካት ካጤኗቸው ሙያተኞች ቀዳሚው ቴን ሃግ መሆናቸውም ታውቋል።
ኔዘርላንዳዊው ቴን ሃግ ከማንችስተር ዩናይትድ ሃላፊነታቸው ከተሰናበቱ ወዲህ በአንዳንድ ክለቦች የአሰልጥነን ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ፈቃደኛ አልነበሩም።
ፈቀደኛ ላለመሆናቸው ምክንያት ያቀረቡትም በውድድር አመት አጋማሽ ሃላፊነት ላለመረከብ መወሰናቸውን በመግለጽ ነው።
አሰልጣኙ በቀጣይ አመት ወደ ስራቸው መመለስ ይፈልጋሉ የሚለው የኪከር ዘገባ፣ የባየር ሊቨርኩሰንን ጥያቄ ሊያጤኑበት እንደሚችሉ ይገልጻል።
ቴን ሃግ ከሊቨርኩሰን በተጨማሪ በዚያው በቡንደስ ሊጋ ተወዳዳሪ በሆነው አርቢ ላይብዚሽም ተፈላጊ ሆነዋል። ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ በጀርመን የስራ ታሪክ ያላቸው ሲሆን በአውሮፓውያኑ ከ2013 እስከ 2015 የባየር ሙኒክን ሁለተኛ ቡድን አሰልጥነዋል።
በ- አልፈሪድ ነስሮ












