የምሽቱ ጨዋታ በመጀመሪያ 45 ደቂቃ አራት ጎሎች የተቆጠሩበት በአስደናቂ ፉክክር የታጀበ ነበር።
እንግዳው ኢንተር በማርከስ ቱራምና ዴንዚል ዱምፍራይስ የ1ኛ እና 21ኛ ደቂቃ ጎሎች ቀድሞ መምራት ቢጀምርም ባርሳ ከ3 ደቂቃ በኋላ በላሚን ያማልና በ38ኛው ደቂቃ በፈራን ቶሬስ ምላሽ ሰጥቶ የመጀመሪያው አጋማሽ 2-2 ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ኢንተር በዴንዚል ዱምፍራስ የግንባር ኳስ በድጋሜ መምራት ችሎ ነበር።
ሆኖም ግን ባለሜዳው ቡድን ባርሳ በአንድ ደቂቃ ልዩነት በራፊና አማካኝነት መልስ ሰጥቷል ምንም እንኳ ጎሏ በእራስ ላይ ተብላ በያን ሶመር ብትመዘገብም።
በጨዋታው ባርሳ በተለይም ወደ ተጋጣሚ ቡድን ሜዳ በእጅጉ ተጠግቶ ለመከላከል ያደረገው ሙከራ ለጎሎች መቆጠር አስተዋጾ ነበረው።
የ72 በመቶ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የነበረው የሀንሲ ፍሊክ ቡድን 9 ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን አድርጎ 3ቱን ወደ ግብነት ቀይሯል።
የመልሶ ማጥቃት የጨዋታ መንገድን ሲተገብር ያመሸው የሲሞኒ ኢንዛጊ ኢንተር በአንጻሩ በዚህ ዕረገድ 3 ሙከራዎችን ብቻ አስመዝግቧል።
ቡድኑ በሄንሪክ ሚኪታሪያን አማካኝነት ያስቆጠራት 4ኛ ጎል በቫር ጣልቃ ገብነት ተሽራበታለች።
ባርሳ ቅዳሜ ዕለት በስፔን ኮፓ ዴል ሬይ የፍጻሜ ጨዋታ ሪያል ማድሪድን ካሸነፈ በኋላ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሰንቆ ያደረገው ግጥሚያ ነበር።
ምሽት ሁለተኛዋን ጎል ያስቆጠረው ላሚን ያማል በውድድር ዓመት ለባርሳ በ35 ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል። 15 ሲያስቆጥር 20 አመቻችቶ አቀብሏል።
የ17 ዓመቱ ስፔናዊ ከምባፔ በኋላ በዚህ መድረክ በ16ቱ ጥሎ ማለፍ፣ በሩብ ፍጻሜና በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ያስቆጠረ ሁለተኛው ታዳጊ ተጫዋችም ሆኗል።
ለፈራን ቶሬስ አመቻችቶ ያቀበለው ብራዚላዊው አጣማሪው ራፊና በበኩሉ በውድድር ዓመቱ በሁሉም መድረኮች በ52 ጎሎች ተሳትፏል፣ 30 አስቆጥሮ ለጓደኞቹ 22 አቀብሏል።
ኢንተር ሚላን በኮፓ ኢታልያና ሴሪ ኤው በተከታታይ 3 ጨዋታዎች አንድም ጎል ሳያስቆጥር ጭምር ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ የቀደመ ብርታቱን መልሶ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ነው።
የመልሱ ጨዋታ በሚቀጥለው ሳምንት ሳን ሲሮ ላይ ይደረጋል።
በ-ይበልጣል ሰውነት












