NBC Ethiopia አልፈሪድ ነስሮ
April 21, 2025
ጠዋት 3፡30 በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የተካሄደው የአዳማ ከተማ እና የመቻል ጨዋታ፣በመቻል 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ለመቻል ሁለቱንም ጎሎቹን አምበሉ ሽመልስ በቀለ ያስቆጠር ሲሆን ነጥባቸውን 35 በማድረስ 6ተኛ ስፍራ ላይ ለመቀመጥ ችለዋል።
በዚሁ ስታዲየም ቀን 9 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ሆኗል። በደረጃ ሰንጠረዥ 33 ነጥብ በመያዝ 11ኛ ስፍራ ላይ የሚገኙት አጼዎቹ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች የተሸነፉት በአንዱ ብቻ ነው። የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ የሚችሉ ከሆነ ነጥባቸውን 36 በማድረስ 6ተኛ ስፍራን ከመቻል ለመረከብ ያስችላቸዋል።
ከወራጅ ቀጠና በ 4 ነጥብ ርቆ 14ተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ድሬዳዋ በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት ነጥብ መሰብሰብ የግድ ይለዋል። ሁለቱም ቡድኖች ለተለያየ አላማ ነጥቡ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ምሽት 12 ሰዓት ባህር ዳር ከተማን ከ መቀሌ 70 እንደርታ የሚያገናኘውም መርሃ ግብር እንዲሁ ተጠባቂ ነው። ባህርዳር 37 ነጥብ በመያዝ ሶስተኛ ስፍራ ላይ የተቀመጠ ሲሆን የዛሬውን ጨዋታ ድል ማድረግ ከቻለ ሁለተኛ ስፍራን ከኢትዮጵያ ቡና ይረከባል።
ወጥ አቋም ለማሳየት የተቸገሩት የጣና ሞገዶቹ፣ ከወራጅ ስጋት ለመዳን እያለሙ ወደ ሜዳ የሚገቡት 70 እንደርታዎች እንደሚፈትኗቸው ይጠበቃል። መቀሌ 70 እንደርታ ከወራጅ ቀጠናው የ7 ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከስጋት ሙሉ በሙሉ ለመላቃቅ ነጥብ ማግኘት ይኖርበታል።













