April 15, 2025
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ሲደረጉ ቀን 9:00 ሰዓት ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና ክለቦች መካከል የሚደረገው ጨዋታ ይጠበቃል።
በሀዋሳ ስታዲየም ግጥሚያቸውን የሚደረጉት ሁለቱ ክለቦች፣ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ በቅርብ ርቀት ይከታተላሉ። ቡናማዎቹ በ36 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በአንጻሩ አጼዎቹ ደግሞ በሶስት ነጥብ ዝቅ ብለው ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ሁለቱ ክለቦች ለ16 ጊዜ ተገናኝተው፣ ፋሲል ከነማ አምስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አራት ጊዜ አሸንፏል። በሰባት ጨዋታዎች ደግሞ ሳይሸናነፉ ነጥብ ተጋርተው ተለያይተዋል።
በ24ኛው ሳምንት ጨዋታ አጼዎቹ ድል ቀንቷቸው የነበረ ሲሆን፣ ቡናማዎቹ ደግሞ ነጥብ ተጋርተው የ25ኛ ሳምንት የዛሬ ግጥሚያቸውን ያደርጋሉ።

በሌላ ጨዋታ ምሽት 12:00 ሰዓት ላይ መቻል ከ አርባ ምንጭ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በ34 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አርባ ምንጮች ጨዋታውን ያሸንፋሉ የሚል ቅድመ ግምት ቢሰጣቸውም፤ ስምንተኛ ደረጃ ላይ በ32 ነጥብ የተቀመጡት መቻሎችም በቀላሉ የሚበገሩ አይደሉም ተብሏል።













