፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ጥቅምት 08 2017| NBC ETHIOPIA- የኢትዮጵያ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ከናይሮቢ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ እና ከአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በኬንያና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን የካፒታል ገበያ ከማሳለጥ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ ካፒታል ገበያ እድገትም ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል።
የዕውቀት ልውውጥ፣ የዓቅም ግንባታ እና በሀገራቱ መካከል ድንበር ተሻጋሪ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት የመግባቢያ ስምምነቱ ከሚያተኩርባቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል ስለመሆናቸው ተገልጿል።

ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው የገለፀው የኢትዮጵያ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የገበያውን እድገት ከማሳለጥ ባሻገር ኢትዮጵያ በአፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ ወሳኙን ሚና እንድትጫወት ያስችላታል ብሏል።
በአፍሪካ ከግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች መካከል በሆኑት ሃገራቱ እያደገ የመጣውን የካፒታል ገበያ ለማስፋት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው የገለፀው የናይሮቢ የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የመግባቢያ ስምምነቱ በሁለቱም ሃገራት ላሉ በዘርፉ ሙዓለ ንዋይ ፈሰስ ለማድረግ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች መልካም ዕድል የሚፈጥር ብሎም ዓለም ዓቀፍ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደሚያግዝ አስታውቋል።


ለኢትዮጵያ አዲስ የሆነው የካፒታል ገበያ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት የገለፀው አይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ለመግባቢያ ስምምነቱ ስኬት ከተቋማቱ ጋር እንደሚሰራ ገልጿል።
በ-መቅደስ ደምስ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












