፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ጥቅምት 01 2017| NBC ETHIOPIA- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በጥቅምት ወር በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ኮንፈረንሶችን ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጓን ተናግረዋል።
ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት በድምቅት መከበራቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ ከፍተኛ የቱሪዝም ፍሰት የተደረገበት እንደነበር ገልጸዋል።
በዓላቱ የማህበረሰብን የአኗኗር ዘይቤ፣ ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ እንዲሁም የሕዝቦችን ትስስር በማጠናከር ባህልን ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ እድል የሰጠ ነው ብለዋል።
ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ ”ከረሃብ ነጻ የሆነ ዓለም” ኮንፈረንስን እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን በመድረኩ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ 1 ሺህ 500 እንግዶች እንደሚሳፉበት ተገልጿል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ስብሰባ ከጥቅምት 5 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም 3ኛው የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ በአዲስ አባባ ከጥቅምት 12 ጀምሮ ይካሄዳል የተባለ ሲሆን ጉባዔው ኢትዮጵያ በሰላምና መረጋጋት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ሚና እንደምታሳይ ተገልጿል።
በ-ሰላማዊት ወንድወሰን












