፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ጳጉሜ 04 2016| NBC ETHIOPIA-የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ በጎንደር ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪ የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሳው ፣የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘውን ጨምሮ የከተማው ከፍተኛ አመራሮች በፒያሳ እየተገነባ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል ።

የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ተሞክሮ ወደ ጎንደር በማስፋት እየተሰራ መሆኑን እና እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ከንቲባዋ የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር አጋዥ ነው ብለዋል ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው የኩሪደር ልማቱ ለከተማችን የስራ ባህልን የሚያዳብር ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል ።
በከተማዋ የኮሪደር ልማቱ ሲጀመር ማኀበረሰቡ ትብብር እያደረገ እንደሚገኝም የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የኮሪደር ልማቱ በቀንም፣ በምሽትም እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት መነሳሳትን እንደፈጠረም አቶ ቻላቸው ገልጸዋል።
አዲስ አበባ እና ጎንደር ከተማ በቀደሙት ጊዜ በልማት ይደጋገፋሉ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በከተማዋ የተጀመረውን የልማት እንቅስቃሴ ለጎንደርም እንዲደርስ በማደረጉ ጎንደር ከተማ ታመሰግናለች ብለዋል።
የፋሲል አብያተ መንግሥት የቅርስ ጥገና ከፍተኛ እንደ አይናችን ብሌን የምንከታተለው ፕሮጀክት በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ በየቀኑ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አቶ ቻላቸው መግለፃቸውን የአሚኮ ዘገባ ያመለክታል፡፡












