የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አብዮተኛ፤ፖለቲከኛ፤የፖለቲካል ሳይንስ አጥኚ ነው፤በታሪክ መዝገብ ላይ ከተከተቡ መሪዎች እስከ አሁንም በአነጋጋሪነቱ ይታወቃል ቭላድሚር ኢሊች ኡሊያኖቭ ወይንም ቭላድሚር ሌኒን
መካከለኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች በቀድሞዋ ሲምብሪስክ በአሁኑ ሊያኖቭስክ ሚያዚያ 22 ቀን በ1870 ነው የተወለደው፡፡ከስምንት እህት እና ወንድሞቹ የቤቱ 3ኛ ልጅ ሆኖ ይህቺን ምድር ተቀላቀለ፡፡
በልጅነቱ የፈጣን አዕምሮ ባለቤት የሆነው ሌኒን ገና በልጅነቱ የታላላቆቹን የሩሲያ ደራሲያን መጽሕፍትን ጠንቅቆ ያነብ ነበር ይባልለታል፡፡በርካታ ጊዜያትን መጻሕፍትን ተሸክሞ ወደ ጫካ እየሄደ ከአያሌ መጻሕፍት ጋር ዝምድናን ፈጥሯል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ጀምሮ የሀገሩን ሩሲያ እና ሌሎች ሀገራትን የፖለቲካ ስርአትም ያጠና ነበር፤የላቲን እና የግሪክ ቋንቋዎችንም እንዲሁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለ የወቅቱን ሳሪዝም እየተባለ የሚጠራውን የንጉሳዊ አምባገነን ስርአትን በመቃወሙ ከትምህርት ገበታው ተባሯል፡፡
ይህ ከምንም ያላገደው ሌሊን መጻህፍት ማንበቡን አዳዲስ ሃሳቦችን መመርመሩን ተያያዘው፤ በተለይም የህግ ጉዳዮችን በጥልቀት በማንበብ እና በማጥናት የህግ ጠበቃ መሆን የሚያስችለውን ፍቃድ እስከማግኘት ደረሰ፡፡
ከዚህ በኋላ ነበር በ1893 ከተወለደባት ከተማ ወደ አሁኗ ሴንት ፒተርስበርግ በመዘዋወር ቀንደኛ የማርክሲዝም አቀንቃኝ እና አክቲቪስት የሆነው፡፡አንዳንዶች የሌኒን ወንድም ሰር አሌክሳንደር ሶስተኛን ለመግደል አሲረሃል በሚል በስቅላት ከተቀጣ በኋላ ነው የወንድሙን ደም ለመበቀል እና የንጉሳዊ ስርአቱን ለመቃወም የተነሳው የሚሉ አሉ፡፡

በ1895 የማርክሲስት ህብረት እንዲመሰረት ከማገዝ አንስቶ የጉልበት ሰራተኞች የዚሁ ቡድን አባል እንዲሆኑም ይመለምል ነበር፤ ፖለቲከኛው ሌኒን ይህንኑ ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት ለእስር ተዳርጓል፤ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ምዕራብ አውሮፓ በመጓዝም አብዮታዊ እንቅስቃሴውን ቀጥሏል፡፡
እ.ኤ.አ በ1902 what is to be done? የተሰኘ በራሪ ወረቀት በማሳተም ሩሲያ የሶሻሊዝም ርዕዮት መከተል እንደሚገባት እና እውን ሊሆን የሚችለውም ፕሮፌሽናል በሆነ አብዮተኛ ፓርቲ በማቋቋም እንደሆነ ሰብኳል፡፡ ኢስካራ እና ብራቭዳ በተባሉት ታዋቂ ጋዜጦቹ አብዮታዊ ሃሳቦችን በመፃፍ በርካቶችን ያነሳሳ ነበር፡፡
በ1903 ሌሎች የማርክሲዝም አቀንቃኞችን ጋር በለንደን በመጣመር Russian Social-Democratic Workers’ Party (RSDWP) መሰረቱ፤በ1905 የሩሲያ አብዮት ከፈነዳ በኋላ ሌኒን ወደ ሩሲያ ተመለሰ፤ አብዮቱ ብዙም ሳይቆይ C-ZAR መሪዎች ዳግም በማንሰራራታቸው በድጋሚ ከሀገረ ሩሲያ እንዲሰደድ ሆኗል፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1914 የተቀሰቀሰውን የአንደኛው የአለም ጦርነትን የኢምፔሪያሊስቶች ጦርነት ነው በሚል ሌኒን ይሟገት ነበር፤እንዳለውም ጦርነቱ ሩሲያን እጅግ ዋጋ ያስከፈላት ዜጎቿ ለረሃብ እና ለሌላ ለበርካታ ችግሮች የዳረጋት፤ በምግብ እጥረት ሳቢያ ዜጎች ሆ ብለው የወጡባት ከዛም ባሻገር ተስፋ የቆረጡ ወታደሮች የህዝቡን ንቅናቄ በመከተል የሳር ንጉሳዊ አገዛዝ እንዲያበቃ እስከማድረግ የደረሰበት ወቅት ሆኖ አልፏል፡፡

በየካቲት ወር ተከስቶ በነበረው በዚህ አብዮታዊ ንቅናቄ ማግስት ሀገሪቱን በሁለት የተከፈሉ አመራሮች ስር እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ በማርክስና በኤንግልስ ጽንሰ ሃሳብ መሰረቱን አድርጎ የሩሲያን ከተሞች ለመለወጥ ይታገል የነበረው ሌኒን በሚከተለው ርዕዮታዊ አለም ሳቢያ፤ተደጋጋሚ እስራት፤ ከሀገሩ እርቆ መኖር ቢዳረግም በስተመጨረሻ ከ15 አመታት መራር ትግል በኋላ በ1917 ህልሙን እውን በማድረግ ወደ መንበረ ሥልጣን መምጣትም ችሏል፡፡
በአንድ አገዛዝ በኮሚኒስት ፓርቲ የምትመራ ሶቪየት ሩሲያን ኋላም ሶቪየት ህብረት መስራች እና መሪ መሆን ችሏል፡፡
ሌኒን የራስን እድል በራስ መወሰን ፣ ትምክህተኞችንና አድርባዮችን መታገል ፣ ለወዛደሮች ቅድሚያ መስጠት ፣ ሰራተኛውንና አርሶ አደሩን ማሳደግ በሚል መሪ ሀሳቦች የህብረት ስራ ማህበርን በማደራጀት፣ኋላቀርነትን የማስቀረት ዘመቻ፣ ታላላቅ ኢንደስትሪዎችን ማቋቋም፣ነጻ የህዝብ ህክምናንና እና ሎሎች ብዙ ሥራዎችን በአብዮት መልክ በሩሲያ ምድር ለመስራት የሞከረ መሪ ነበር ይሉታል፡፡
በሌላ በኩል በቀዩ ጦሩ ሚሊዮኖች እንደ ቅጠል እንዲረግፉ ምክንያት የሆነ፤ የእርሱን ሀሳብ መቀበል ወይንም ሞት የሚል መርህ ተከታይ፤ ጨካኝ እና ገዳይ ነው የሚሉትም በሌላ ጎራ ይደመጣሉ፡፡
ሌኒን በደቡባዊ ሞስኮ በሚገኘው ሀመር እና ሲክል በተባለ የጦር መሳሪያ ፋብሪካ ንግግር አድርጎ በመውጣት ወደ መኪናው ለመግባት እያቀና ሳለ ፋኒ ካፕላን የተባለች እንስት ስሙን በመጥራት ዞር ሲልላት 3 ጥይቶችን አከታትላ ታዘንብበታለች፡፡
አንደኛው በለበሰው ኮት ላይ ሲያርፍ ቀሪ 2ቱ ግን በአንገቱ እና በሳንባው ላይ ያርፋሉ፤ በዚህም ከባድ ቁስለት እና ስቃይ ውስጥም ቢገባም ከሞት ተርፏል፡፡በወቅቱ ከጥቃቱ ቢያገግምም ዳግም ጤናው ሊመለስ ግን አልቻለም፤ የተተኮሱበት ጥይቶች ለስትሮክ ዳርገውታል፤ በመጨረሻም በ1924 ታሞ ከዚህ አለም በሞት እንዲለይ ምክንያት ሆኖበታል፡፡
በ-አብስራ ሚሊዮን












