፨ ፨ ፨ ፨ ፨፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ነሐሴ 27 2016| NBC ETHIOPIA-አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዲስ ተማሪዎች ቅበላ አሰራርን ከ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ ሊያደርግ ነው። ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያው የመንግስት ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ ከ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ከመንግስት ምደባ ውጪ በራሱ መስፈርት አወዳድሮ እንደሚቀበል የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ገለጹ።
ይህም ዩኒቨርሲቲውን የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እና ልዩ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ማስተማሪያ ያደርገዋል ነው የተባለው ። መንግስት በትምህርት ሴክተር ላይ ያጋጠመውን የጥራት ችግር ለማከም ዘርፈ ብዙ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ እና በ2017 የትምህርት ዘመን ወደ ስራ የሚገባው አዲስ የተማሪዎች ቅበላ ስርዓት ከነዚሁ ስራዎች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ተናግረዋል። አሰራሩ በመንግስት ወጪ የሚሸፈን የትምህርት እድል (ስኮላርሺፕ) እና በግል ወጪን በመሸፈን የተማሪዎች ስብጥር በጠበቀ መልኩ ማስተናገድ እንዲያስችል ተደርጎ የተቀረፀ ነው።

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ቅበላ ስርዓት ለቅደመ ምረቃና ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች በተቀረፀው ፖሊሲ የሚተገበር ሆኖ ለሴቶች፣ለአካል ጉዳተኞች እና ለታዳጊ ክልል ለሚመጡ ተማሪዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ፍትሀዊነቱ ይረጋገጣል ሲሉ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል ።
አዲስ ይተገበራል በተባለው የቅበላ አሰራር በ2014፤ 2015 እና 2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ወስደው የማለፊያ ነጥብ ያገኙ ተማሪዎች የሚወጣውን መስፈርት ታሳቢ አድርገው በዩኒቨርሲቲው ፖርታል https://portal.aau.edu.et መመዝገብ የሚችሉ መሆኑን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።
በ- የአብስራ ብርሃኑ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Website – https://nbcethiopia.com/news/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












