፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 21 2016| NBC ETHIOPIA-የጊዜው መዘመንን ተከትሎ ተመራማሪዎች ለበርካታ የጤና እክሎች መፍትሔ የሚሆኑ ግኝቶችን ለዜጎች በተለያዩ ጊዜያት እንካችሁ ሲሉ ቆይተዋል፡፡
ሆኖም ተመራማሪዎችን በእጅጉ የፈተኑና እስካሁንም መፍትሔ ያልተገኘላቸው የተለያዩ በሽታዎች ይገኛሉ፡፡
ለበሽታው መድሃኒት ብሎም መንስኤን ማግኘት አዳጋች ከሆኑ በሽታዎች መካከል በህክምና አጠራሩ ፕሮጄሪያ በመባል የሚታወቀው በሽታ ይገኝበታል፡፡
ፕሮጄሪያ የተሰኘው በሽታ ጨቅላ ህጻናትን የሚያጠቃ ሲሆን ህጻናት ከእናታቸው ማህጸን ከወጡበት ጊዜ አንስቶ የፊታቸውም ሆነ የሰውነታቸውን ገጽታ በእጅጉ የሚቀይር የበሽታ አይነት ነው፡፡
ይህን መሰሉ የበሽታ አይነት በአለማችን እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡በዚህ በሽታ ተጋላጭ የሚሆኑ ህጻናት ቁጥር ከስምንት ሚሊየን ህጻናት መካከል አንዱ መሆኑን በዘርፉ የሚወጡ የጥናት ውጤቶች ያሳያሉ፡፡

ፕሮጄሪያ በተሰኘው በሽታ የሚጠቁ ህጻናት በእድሜ የመቆየት እድላቸው እስከ 13 አመት ድረስ ብቻ መሆኑንም ይህ የጥናት ውጤት የሚያሳይ ሲሆን ይህንን የእድሜ ክልል የሚሻገሩ ህጻናት ቁጥር በእጅጉ አናሳ ነው፡፡
ከዚህ በሽታ ጋር በተያያዘ ረጅም እድሜ ያስመዘገበችው ቲፋኒ የተሰኘች ግለሰብ ስትሆን በፈረንጆቹ 2023 45ኛ አመቷን አስቆጥራለች፡፡ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በዚህ በሽታ እኩል ተጠቂ መሆናቸውንም ነው የጥናት ውጤቶች የሚያመላክቱት፡፡
የዚህ በሽታ መነሻ መንስኤ ተብሎ በዘርፉ አጥኚዎች የሚቀርበው የልጁ ሰውነት በፍጥነት እርጅና እንዲፈጠር የሚያደርገው ያልተለመደ የጄኔቲክ መታወክ እንደሆነ ነው፡፡
በሴላችን ውስጥ የሴላችንን ደህንነት የሚጠብቀው ላሚን ኤ የተሰኘው ፕሮቲን በተለያዩ ምክንያቶች ፕሮጂሪን ወደ ተባለ ፕሮቲን በሚቀየርበት ጊዜ ላሚን ኤ የተሰኘው ፕሮቲን ዋነኛ ግልጋሎቱን መስጠት የሚያቆም ሲሆን በዚህን ወቅት ሴላችን መጨማደድ ይጀምራል፡፡

አዲስ የሚወለዱ ሕጻናት በሚወለዱበት ጊዜ ጤናማ ሆነው ሊታዩ ይችላሉ፡፡በመጀመሪያው አመት እንደ የዝግመተ እድገት፣ የስብ ቲሹ መጥፋት ብሎም የፀጉር መርገፍ የመሳሰሉ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራሉ፡፡
ነገር ግን በአብዛኛው ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባለው የሕይወት ዘመናቸው ያለጊዜያቸው የእርጅና ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራሉ።
በዚህን ወቅት የእድገታቸው ፍጥነት ከመቀነሱም በተጨማሪ ክብደታቸውም ቢሆን አይጨምርም፡፡በአብዛኛዎቹ በፕሮጄሪያ ተጠቂ ህጻናት ውስጥ የልብ ችግሮች ወይም ስትሮክ የመሳሰሉ በሽታዎች ሊስተዋሉ ይችላሉ፡፡ይህ ችግር ያለባቸው ህጻናት ምንም እንኳን ከተለመደው በተለየ መልኩ ገጽታ ቢኖራቸውም የማሰብ ችሎታቸው ግን እንደማይጎዳ ይነገራል፡፡

ለዚህ በሽታ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት መድኃኒት ማግኘት ያልተቻለ ቢሆንም አዳዲስ የሚወጡ ጥናቶች ችግሩን ለመቆጣጠር ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኝተዋል ተብሏል፡፡
በአፍ የሚሰጠው ሎናፋርኒብ የተሰኘ መድሃኒት ችግሩን ለመቆጣጠር እንደሚረዳ የተመላከተ ሲሆን ፕሮጄሪያንና መሰል ፕሮቲኖች በሴሎች ውስጥ እንዳይከማቹ የሚረዳ ነው ተብሏል፡፡
ይህንን በሴሎች ውስጥ መከማቸትን መከላከል በፕሮጄሪያ ውስጥ የሚከሰቱትን የሕመም ምልክቶች እድገት ሊቀንስ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን ይህም አንዳንድ ልጆች ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ ያስችላቸዋል።ፕሮጄሪያ ሪሰርች ፋውንዴሽን እንደገለጸው ከሆነ በዓለም ላይ በዚህ ችግር ተጠቂ የሆኑት ህጻናት ቁጥር በእጅጉ ጥቂት የሚባል ነው፡፡ተጠቂ የሆኑ ህጻናት ትልቅ ጭንቅላት፣ ትንሽ አፍና አገጭ፣ ጠባብ አፍንጫና ትልቅ አይኖች ያላቸው የፊት ገጽታ ሲኖራቸው ራሰ በራነት የጥርስና የመገጣጠሚያዎች መዛባት ከሚታዩ ምልክቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
አንድ ልጅ ከፕሮጄሪያ ጋር የወለዱ እንደሆነ ለሁለተኛ ጊዜ ከፕሮጄሪያ ጋር የመውለድ እድላቸው ከአጠቃላይ ህዝብ አንጻር በተወሰነ መልኩ ከፍ ያለ ቢሆንም የመከሰት እድሉ ግን ጠባብ ነው፡፡እንደ የአኗኗር ዘይቤ ወይም የአካባቢ ጉዳዮች ያሉ የታወቁ ምክንያቶች የሉም ፕሮጄሪያ የመውለድ ወይም ፕሮጄሪያ ያለው ልጅ የመውለድ አደጋን ይጨምራሉ።












