
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ጥራታቸውን ሳይጠብቁ ወደ ገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ላይ እያከናወነ ያለውን የቁጥጥርና ክትትል ስራን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ እየሰጠ ይገኛል።
ባለስልጣኑ የቅኝት ስራዎችን ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በትብብር በማካሄድ ጥራቱን ያልጠበቀ 13 ሺህ ኩንታል የገበታ ጨው ወደ ህብረተሰቡ ከመሰራጨቱ አስቀድሞ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ነጋሽ ስሜ ተናግረዋል።
አዮዲን የሌለው እንዲሁም ያልታጠበ የገበታ ጨውን ለገበያ ሊያቀርቡ ሲዘጋጁ የነበሩ ግለሰቦች ወደ ገበያ ከመሰራጨታቸው አስቀድሞ በተደረገው የክትትል ስራ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የገለፁት።
በቁጥጥር ስር የዋሉት አፋር፣ አፍዴር ወለላ እና በርዋቅ የሚል ስያሜ ያላቸው የጨው ምርቶች መሆናቸው ተገልጿል።
ምርቶቹ የተገኙት በሸገር ከተማ አስተዳደር ፉሪ ክፍለ ከተማ ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ ሲሆን በግለሰቦቹ ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በምግብ ዘይት ላይ በተከናወነ የቅኝት ስራ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ዘይቶች መገኘታቸው ተገልጾ ከስልሳ እስከ ሰባ የሚደርሱ ህጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸው ተጠቁሟል።
በ – አክረም ኑርያ












