፨ ፨ ፨ ፨ ፨
የዓለማችን ልጥጦች እና ዝነኞች ለምን እና እንዴት ሳይባሉ ያሻቸውን የሚያደርጉባት የዓለማችን ቅንጡዋ ሀገር ናት።
በአለም አቀፍ ደረጃ በማራኪው ገጽታዋ፣ በውብ ቤተመንግስቶቿ፣ በአስደናቂ ሙዚየሞቿ፣ በልዩ የአትክልት ስፍራዎቿ ፣በቅንጡ ሆቴሎቿ ፣በባህር ዳርቻዎቿ እንዲሁም የቅንጡ ህይወት በሚኖሩ ነዋሪዎቿ ይበልጡኑ ትታወቃለች ሞናኮ፡፡
ሞናኮ በመሬት ስፋትም ሆነ በሕዝብ ብዛት በዓለም ላይ ካሉ ትናንሽ አገሮች አንዷ ናት።በምዕራብ አውሮፓ በፈረንሳይ ሪቪዬራ ላይ የምትገኘዋ ሞናኮ የቆዳ ስፋቷ 2.02 ስኩዌር ኪሎ ሜትር (0.78 ካሬ ማይል) ብቻ ነው። ይህም ዓለማችን ላይ ከቫቲካን በመቀጠል ሁለተኛዋ የዓለም ትንሿ ሀገር ናት ይላሉ በዙሪያዋ የሚወጡ መረጃዎች።
ሞናኮ የዓለማችን ባለጠጎች መኖሪያ ናት።እ.ኤ.አ በ2023 የቅንጦት ህይወት የሚኖርባት ሞናኮ አጠቃላይ የህዝብ ብዛቷ 38,367 ነበር። ከሞናኮ ህዝብ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ሚሊየነር እንደሆነ ይገመታል። በሞናኮ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የፈሰሰበት የአልማዝ መአድን አጊጠው ቢወጡም ዞር ብሎ የሚያዮት ላይኖር ይችላል ይህ ሞናኮ ነው በቃ የአለም ምርጥ ሀብታሞች የሚምነሸነሹበት ስፍራ።

በሞናኮ የሄሊኮፕተር ጉዞ የተሽከርካሪ ያህል ቀላሉ የመጓጓዣ ዘዴ ነው። ለነጋዴዎች፣ ለታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም ለባለጸጋዎች ቀልጣፋ የመጓጓዣ ዘዴ በመሆኑ ሄሊኮፕተር ተመራጭ ነው።
የሄሊኮፕተር አገልግሎቶች ሞናኮን ከፈረንሳይ ኒስ ኮት ዲዙር አውሮፕላን ማረፊያ እና ሌሎች በፈረንሳይ ሪቪዬራ ከሚገኙ መዳረሻዎች ጋር እንዲገናኙ የተደረገ ነው።
የሪል እስቴት ቤቶች በጣም ውድ ከሆኑባቸው ሀገራት መካከል ሞናኮ ተጠቃሽ ናት። ካለው የመሬት አቅርቦት እጥረት እና ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ እንዲሁም ሀገሪቱ ላይ ባለው ልዩ የቅንጦት ገበያ ምክንያት በዓለም ላይ በጣም ውድ ከሚባሉ ሀገሮች ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል።
በሞናኮ የእግረኞችን እንቅስቃሴ ለማመቻቸት ነው በሚል በዋና ከተማዋ ውስጥ በተወሰኑ ቦታዎች ነፃ አሳንሰሮች እና መወጣጫዎች አሉ።እነዚህ አሳንሰሮች የሚገኙት ኮረብታዎች ባሉበት አካባቢ ሲሆን ይህም ለተለያዩ የከተማው ቦታዎች ምቹ መዳረሻን ለመፍጠር እና እግረኞች የከተማውን ገጽታ በቀላሉ መጎብኘት እንዲችሉ ለማድርግ ታስቦ ነው።

በሀገሪቱ ፈጽሞ ከተከለከሉ ጉዳዮች መካከል ቁማር መጫወት ነው። ይህ ድርጊት በህግ ሳይቀር የተከለከለ ነው፡፡ ይህንን ገደብ መጣል ያስፈለገው ዜጎች የቁማር ሱስ ሊያስከትልባቸው ከሚችለው አሉታዊ ተፅእኖዎች ለመጠበቅ ስለመሆኑ ይነገራል።
ሞናኮ በዓለም ላይ ካሉ ዝቅተኛ ወንጀል ከተመዘገበባቸው ሀገራት አንዷ ናት።ከፍተኛ የሆነ ደህንነት እንዳላት የሚነገርላት ሞናኮ በአማካኝ ለ73 ነዋሪዎች አንድ የፖሊስ አባል አላት።
ሞናኮ ለነጋዴዎች፣ ለታዋቂ ሰዎች እና ለባለሃብቶች ኑሮ ተመራጭ እንድትሆን ያደረጋት ዋነኛ ምክንያት ምንድ ነው ቢሉ የገቢ ታክስ አለማስከፈሏ ነው። የሞናኮ ነዋሪ እስከሆኑ ድረስ ግዛቲቱ ለዓለም አቀፍ ገቢዎች የግል የገቢ ታክስ አትጥልም።
ሞናኮ ህዝቦቿ የአለማችን ከፍተኛ የሞት ጣራ መጠንን የያዙ ናቸው። በአማካኝም 85 ዓመት የእድሜ ጣራ አላት ።የነዋሪዎች አማካይ ዕድሜ ወደ 44 ዓመት አካባቢ ነው, እና 14% የሚሆነው ህዝብ ከ 75 ዓመት በላይ ነው።ይህ የሆነበት ምክንያት በሀገሪቱ ያለው የጤና እንክብካቤ ጥራት፣ ምርጥ የአመጋገብ ስርዓት የሚከተሉ ሃብታሞች የሚኖሩባት በመሆኗ እንደሆነ ይነገራል።
ሞንቴ ካርሎ ካሲኖ በሞናኮ ውስጥ በጣም ታዋቂ፣ የከተማዋ ውበት እና ድምቀት የሆነ ስፍራ ነው።በርካታ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችም ይህንን ቦታ ለመጎብኘት ወደ ስፍራው ያቀናሉ።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የአለም ዲታዎች በዚች ሀገር በነጻነት ይኖራሉ፣ በአለም ዙሪያ በምጡቅ አእምሮዎች ዲዛይን የተደረጉ ውድ ምርቶች በዚህች ሀገር አገልግሎት ላይ ይውላል
ስለምትንቀሳቀሱበት ስፍራ ፍጹም ነጻነት ይሰማችሁ ስትል ሞናኮ ድብቅ ካሜራዎች እና አዳኝ የካሜራ ባለሙያዎች ድርሽ እንዳይሉም ከልክላለች፡፡
በ- ሃይማኖት ወርቁ












