፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 29 2016| NBC ETHIOPIA- በአለም ዙሪያ በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ማትረፍ የቻለው እና ለረጅም አመታት ተወዳጅ ሆኖ የቆየው ፍሬንድስ (Friends) የተሰኘው ተከታታይ አስቂኝ ድራማ የመጨረሻው ክፍል ለእይታ የበቃው እ.ኤ.አ 2004 በትላንትናው ዕለት ነበር ፡፡
የአሜሪካንን የቴሌቭዥን ተከታታይ ደራማ ዘውግ ለበርካታ አመታት ተቆናጦ የቆየው ፍሬንድስ የተሰኘው አስቂኝ ድራማ በመላው አለም እስካሁንም ድረስ ተወዳጀ ሆኖ መቆየት ችሏል ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመልካቾች በፊልሙ ውስጥ ያሉትን ገጸባህሪዎች ዛሬም ድረስ እንደቤተሰብ ይመለከቷቸዋል፡፡
በዴቪድ ክሬን እና በማርታ ካውፍማን ተጽፎ እ.ኤ.አ በ1994 ለመጀመሪያ ጊዜ ስርጭቱን የጀመረው ሲትኮሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ ችሏል፡፡
ይህ ተከታታይ አስቂኝ ድራማ የኒውዮርክ ነዋሪ በሆኑ በሀያዎቹ እና ሰላሳዎቹ እድሜ ክልል ወስጥ በሚገኙ ሮስ፣ሞኒካ ፣ ቻንድለር፣ ፊቢ፣ ሬቸል እና ጆዊ በተባሉ ስድስት ጓደኛሞች ዙሪያ የሚያጠነጥን ታሪክ አለው፡፡
እነዚህ የተለያየ የህይወት መንገድ ያላቸው ስድስቱ ጓደኛሞቹም በየዕለቱ የሚገጥሟቸውን የህይወት ውጣ ውረድ ፣ የፍቅር እና የቤተሰብ ገጠመኞችን እና የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚያቀርቡትን ሀሳብ በሳቅ እያዋዛ ለተመልካች የሚያደርስ ሲትኮም ነው፡፡

ገፀባህሪዎቹ የየራሳቸው የተለያየ ሞያ እና ህልም ያላቸው ሲሆን እሱን ለማሳካት በሚያደርጉትን ሩጫ ፣ጓደኝነት፣ መተሳሰበን፣ መደጋገፍን እንዲሁም በርካታ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ቸግሮችን በሳቅ እያዋዛ የሚያቀርብ ነው ፡፡
አንዳድ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም ድራማው ሰዎችን ከማዝናናት ባሻገር በተለያዩ ማህበረሰቦች ላይ የባህል ተጽእኖ እስከማሳደር ችሏል፡፡
ገጸባህሪያቱ የሚጠቀሙት አዳዲስ ቃላት በማህበረሰቡ ዘንድ በስፋት አገልገሎት ላይ ይውሉ ነበር፡፡ በዚህም የእንግሊዘኛ ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳሳደረ በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ተመራማሪዎች ያደረጉት ጥናት ያመላክታል፡፡
በድራማው ላይ የሚገኙት ገጸባህሪያት የሚጠቀሙት የጸጉር ቁርጥ ሳይቀር በአለም አቀፍ ደረጃ በበስማቸው ተሰይሞ ብዙዎች ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡
በዚህ ያላበቃው የሲትኮሙ ተጸእኖ ለበርካቶችም የገቢ ምንጭ መሆን ችሏል፡፡
የተዋንያኑ ምስል የታተሙባቸው ልብሶች እና የተለያዩ ቁሳቁሶች አሁንም ደረስ ገቢን እያስገኙ ይገኛሉ ፡፡ ከዚም ባሻገር በድራማዉ ላይ የታዩትን አፓርታማ ቤቶች ገጽታ በማስመሰል በርካታ ቤቶች ተሽጠዋል፡፡
በአስር ምዕራፎች እና 236 ክፍሎች ተከፋፍሎ ለአስር አመታት በከፍተኛ ተቀባይነት በቴሌቭዥን መስኮት ሲተላለፍ የቆየው ሲትኮሙ ታዋቂውን የኢሚ አዋርድ ስድስት ጊዜ ማሸነፍ የቻለ እና በተለያቱ ዘርፎችም በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ በወቅቱም በአማካኝ በሳምንት 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ተመልካቾች እንደነበሩት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በ2015 በኔትፍሊክስ ድጋሚ መታየት በመጀመሩ እንደ አዲስ መነጋገሪያ መሆን የቻለ ሲሆን ኔትፍሊክስም ለሲትኮሙ በአመት 30 ሚሊዮን ዶላርን ከፍሏል፡፡ዘ ላስት ዋን የተሰኘው የሲትኮሙ የመጨረሻ ክፍልም ሀያ አመታት በፊት በትላንትናው ቀን ነበር አየር ላይ የዋለው ይህንንም ክፍል ከ 52 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል፡፡
ከበርካታ ዓመታት በኋላ በፊልሙ ላይ የሚተውኑት ስድስቱ ተዋናዮች ፍሬንድስ ሪዩኒየን በሚል በተዳጋጋሚ ተገናኝተዋል፡፡
ፍሬንድስ ለተመልካች ከቀረበ ከሶስት አስርት አመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆነውም አሁንም ድረስ በርካታ አለም አቀፍ ተመልካቾች አሉት፡፡ ተዋንያኑም በድራማው ላይ እንደሚታየው በእውነተኛው አለም የልብ ጓደኛሞች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ቻንድለር የተሰኘውን አስቂኝ ገጸ ባህሪ በመጫወት ዝናን ያተረፍው ማቲው ፔሪ ከዚ አለም በሞት በተለየበት ወቅትም የበርካቶች ልብ ተሰብሮ ነበር፡፡
በ- የአብስራ ብርሃኑ












