፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 14 2016| NBC ETHIOPIA- በህንድ ፊልም ኢንደስትሪ ያስጨበጨበች እና የተመሰከረላት ናት፡፡ ህንዳዊቷ ዝነኛ የፊልም ተዋናይት፣ሞዴል፣ ሙዚቀኛ እና የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ፕሪያንካ ቾፕራ፡፡
ፕሪያነካ በህንድ የጦር ሰራዊት ውስጥ የህክምና ባለሞያዎች ከነበሩ ቤተሰቦች እ.ኤ.አ በ1982 ነበር በህንድ ጃምሼድፑር የተገኘችው፡፡
ፕሪያንካ በሊያማርኪኒ የሴቶች ትምህርት ቤት ትምህርቷን እየተከታተለች ለተጨማሪ ትምህርት ወደ አሜሪካ ቦስተን ማሳቹሴት አቀናች፡፡
ለ3 ዓመታት በአሜሪካ ከቆየች በኋላ፣ ወደ ህንድ ተመልሳ በባሬሊ ከሚገኘው የጦር ሰራዊት ትምህርት ቤት ትምህርቷን አጠናቃለች።
ቾፕራ ወደ ሀገሯ ከተመለሰች ከወራት በኋላ በ18 ዓመቷ የ2000 የሚስ ወርልድ ውድድር አሸናፊ መሆን ቻለች፡፡ ያኔ ነው የፊልም ኢንደስትሪውን የመቀላቀል በር የተከፈተላት፡፡
ውድድሩን ማሸነፏን ተከትሎ ወደ ህንድ ፊልም ኢንዱስትሪ ለመቀላቀል የቀረበላትን ጥያቄ ተቀበለች። የመጀመሪያ ትወናዋን የጀመረችው ታማዝሃን በተሰኘ ፊልም በ2002 ነበር፡፡ በመቀጠልም በ2003 The Hero: Love Story of a Spy በተሰኘ በወቅቱ ተወዳጅነትን ባተረፈ ፊልም ላይ ተሳትፋ የአመቱ ምርጥ ረዳት ተዋናይነትን ሽልማት አገኘች፡፡

በ2004 ሙጅሴ ሻዲ ካሮጊ በተሰኘው ፊልም መሪ ሴት ተዋናይት በመሆንም ተጫውታለች፡፡ ፕሪያንካ በ2008 በአንዲት የሞዴል ህይወት ላይ የሚያተኩረውን ፋሽን የተሰኘ ፊልም ላይ ባሳየችው የትወና ብቃት የብሄራዊ ፊልም ሽልማት እና የፊልም ፌር አዋርድ ፎር ዘ ቤስት አክተረስ ሽልማትን በምርጥ ተዋናይት አሸንፋለች። በበርካታ ፊልሞች የተለያዩ ገፀ-ባህሪያትን በማሳየትም ተጨማሪ አድናቆትን አግኝታለች፡፡ በናሽናል ፊልም አዋርድ ላይ ጨምሮ በበርካታ አዋርዶች ላይ ከ88 በላይ ሽልማቶችን ማግኘት ችላለች፡፡
ከ2015 እስከ 2018 የዘለቀው Quantico የተሰኘው ተከታታይ ድራማ ይበልጥ ብቃቷን ያስመሰከረችበት ነበር፡፡ከፊቷ ሳቅ የማይለየው ተወዳጇ ተዋናይት ፕሪንካ በህንድ ቦሊዩድ እና ሆሊዩድ አሻራቸውን ከፍ ካደረጉ የህንድ ፈርጦች መካከል ቀዳሚዋ ናት፡፡ ከፊልም ተዋናኝነት በተጨማሪም 9 ፊልሞችን ፕሮዲዩስ አድርጋለች፡፡
ፕሪያንካ ተዋናይት ብቻ ሳትሆን፣ ሙዘቀኛም ናት፡፡ ሶስት ነጠላ ዜማዎችን በመልቀቅ እውቅናዋን ከፍ አድርጋለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2016 ታይምስ በዓለም ላይ ካሉ 100 ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አንዷ ብሎ ሰይሟታል፡፡ በቀጣዮቹ ሁለት አመታትም ፎርብስ በዓለም ካሉ 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ተርታ አስፍሯታል፡፡ በ2022 ደግሞ በቢቢሲ 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ተርታ ተመዝግባለች፡፡
ከ2006 ጀምሮ ከዩኒሴፍ ጋር በርካታ የበጎ ስራዎችን ስትሰራ የቆየችው ፕራንካ እ.ኤ.አ 2016 የዩኒሴፍ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆና ተሹማለች። በበርካታ ሀገራት እየተዘዋወረችም የበጎ ስራዎችን ትሰራለች፡፡ ከዓመታት በፊትም ኢትዮጵያ መጥታ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2018 ፕሪያንካ ከአሜሪካዊ ዘፋኝ እና ተዋናይ ኒክ ዮናስ ጋር በትዳር ተሳስራ በ2022 የመጀመሪያ ሴት ልጃቸውን አግኝተዋል፡፡
ታዋቂዋ የቦሊውድ እና የሆሊውድ ተዋናይ ፕሪያንካ ቾፕራ የግል ህይወት ጉዞዋን እና ልምዷን ለአድናቂዎቿ ለማካፈል የህይወት ታሪኳ ላይ ያጠነጠነ “unfinished” የተሰኘ መፀሀፏን አጋርታለች። በመፀሃፉ በህንድ ስለነበራት የልጅነት ጊዜዋ፣ ወደ ፊልም ኢንደስትሪ ስለገባችበት አጋጣሚ፣ ወደ ስኬት ስለደረሰችበት መንገድና ሌሎች ተሞክሮዎቿን አንስታለች።

የ41 ዓመቷ ፕራንካ ለብዙ ሴቶች ምሳሌ የምትሆን ብርቱ እንስት ናት፡፡ በሴቶችና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ታደርጋለች፡፡ በተለያዩ መድረኮች የምታስደምጣቸው አነቃቂ ንግግሮች ለብዙዎች ጉልበት የሚሆኑ ናቸው፡፡
ከሰሞኑ ፕሪያንካ በኢንስታግራሟ ባጋራችው መልዕክት፣ ከባለቤቷና ከልጇ ጋር የህንድን ሀያማኖታዊና ባህላዊ ስፍራዎች ከጎበኘች በኋላ ፣በሚቀጥለው የሆሊውድ ፊልም ለመቀረጽ መመለሷን ለአድናቂዎቿ አሳውቃለች፡፡
በህንድ ፊልም ኢንዲስትሪ ያስጨበጨበች እና የተመሰከረላት ናት፡፡ ህንዳዊቷ ዝነኛ የፊልም ተዋናይት፣ሞዴል፣ ሙዚቀኛ እና የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ፕሪያንካ ቾፕራ፡፡












