አዲስ አበባ | ጥር 14፤ 2016| NBC ETHIOPIA – ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 በጀት አመት የመጀመሪያ መንፈቅ አመት 42.89 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል ።በዚህም የእቅዱን 98በመቶ ማሳካት መቻሉንና በግማሽ አመቱ 11 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል ።
ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 በጀት አመት የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት፣ የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ለማሻሻል ፣ የኔትወርክ አቅምን ለማሳደግ ፣የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን ለማስፋትና ለማሻሻል ሰፊ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል ።
በመንፈቅ አመቱ አጠቃላይ የደንበኞች ብዛት 74.6 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 71.7ሚሊዮን የሞባይል ድምፅ ፣36.4 ሚሊዮን የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት እንዲሁም 688.3ሺ የመደበኛ ስልክ ተጠቃሚ መሆናቸው ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል ።
የኔትወርክ ሽፋንና አቅምን ከማሳደግ አንጻር ኩባንያው የማስፋፊያ ስራዎች የሰራ ሲሆን 232 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተገንተዋል ተብሏል ።በዚህም መሰረት1.9 ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞች የሚያስተናግድ አቅም መፈጠሩንና አጠቃላይ የሞባይል ኔትወርክ ደንበኛ የማስተናገድ አቅሙን 81 ሚሊዮን ለማድረስ ተችሏል ሲሉ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ፍሬህወት ታምሩ ጠቁመዋል ።
በበጀት አመቱ የገጠር ወረዳዎች የሞባይል ተጠቃሚነት ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን በ10 ክልሎች ፣ በ41 ወረዳዎች ፣229 ሺህ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችሉ 41 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተተክለው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውም ተገልጿል ።
ከ41 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ባሉት ቴሌብር አማካኝነት በመንፈቅ አመቱ 910.7 ቢሊዮን ብር ግብይት ማካሄድ ተችሏል ።
በሰላማዊት ወልደገሪማ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












