
አዲስ አበባ |የካቲት 04 2015 | NBC ETHIOPIA- ወደር የማይገኝለት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ውድድር ታሪክ በ1950ዎቹ የተጀመረ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሸገር ደርቢ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዋነኛ አካል ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ ለ45ኛ ጊዜ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው፡፡
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ዛሬ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰአት የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
በነዚህ 44 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 21 ጊዜ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና 7 ጊዜ አሸንፏል፤16 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።88 ግቦች ሲቆጠሩ፤ቅዱስ ጊዮርጊስ 60 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና 28 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ ሰባት ጊዜ አሸንፏል። አንድ ጊዜ ተሸንፏል።
አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።28 ጎል ሲያገባ የተቆጠረበት 7 ብቻ ነው። በ21 የግብ ክፍያ በ25 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮጵያ ቡና 12 ጨዋታዎችን አድርጎ አምስቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። 16 ግቦችን አስቆጥሮ 14 ግቦችን ተቆጥረውበታል። በሁለት የግብ ክፍያ በ17 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኢትዮጵያ ቡና በውጤት ማጣት ምክንያት አሰልጣኙን ተመስገን ዳናን ማሰናበቱ የሚታወስ ነው።ዮሴፍ ተስፋዬ ቡናማዎቹን በጊዜያዊነት በማሰልጠን ላይ ይገኛል።
በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚደረገውን “የሸገር ደርቢ” ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
የዚህ የረጅም ጊዜ የውድድር ባህል አካል መሆን እና ጨዋታውን በስታዲየም ማየት በህይወት ዘመን አንድ ጊዜ እድል ነው።
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት
ሃና ተሰማ









