
አዲስ አበባ |የካቲት 06 2015 | NBC ETHIOPIA- የአሜሪካ ጦር በዚህ ወር ለአራተኛ ጊዜ በራሪ አካል በሰሜን አሜሪካ ሰማይ ላይ መትቶ ጣለ፡፡ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ካናዳ ድንበር አቅራቢያ በራሪ አካል መታየቱን ተከስቱ በሰጡት ትዕዛዝ መሰረት ትናንት እሁድ ተመቶ ወድቋል።
ፔንታጎን በመግለጫው ይህ በራሪ አካል ሲበር የነበረው በ20ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ስለነበረ ከመንገደኞች የአውሮፕላን በረራ ትራፊክ ፍሰት ላይ ጣልቃ ሳይገባ አይቀርም ብሏል።
የአሜሪካ ጦር ይህ በራሪ አካል ቅዳሜ ዕለት ሞንታና በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች በላይ ሲበር እንደተገኝ እንዲሁም ሰው አልባው በራሪ በሆነው ኤፍ-16 በተሰኘ ጀት በሚሳኤል ተመትቶ መውደቁን ጦሩ ጨምሮ አስታውቀዋል፡፡
ይህ ክስተት በሰሜን አሜሪካ በረዥም ከፍታ ላይ እየበረሩ የሚገኙ በራሪ አካላት ጉዳይ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ያጫረ ሆኗል።
ከ10 ቀናት በፊት የቻይና የስለላ በራሪ አካል ነው የተባለው ፊኛ በአሜሪካ ሰማይ ላይ ለቀናት ሲበር ተመትቶ መውደቁ ይታወሳል።
ይህች ፊኛ ተመትታ ከወደቀች በኋላ የአሜሪካ ተዋጊ ጀቶች ሦስት ከፍተኛ የአየር ክልል ላይ ሲበሩ የነበሩ በራሪ አካላትን መትተው ጥለዋል።
አርብ ዕለት በአላስካ ግዛት አንድ በራሪ አካል ተመትቶ የወደቀ ሲሆን ተመሳሳይ በራሪ አካል ደግሞ ቅዳሜ ዕለት በሰሜን ምዕራብ ካናዳ ተመትቶ ወድቋል። አሜሪካ እና ካናዳ ተመትተው የወደቁ በራሪ አካላት ስብርባሪዎችን እየፈለጉ ይገኛሉ።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ስለነዚህ ሦስት የበራሪ አካላት ምንነት እና ዓላማ እስካሁን ያሉት ነገር የለም። ይሁን እንጂ የዋይት ሃውስ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ቃል አቀባይ ሦስቱ በራሪ አካላት መጀመሪያ ላይ ተመትታ ከወደቀችው ፊኛ በመጠን በጣም ያነሱ እና በቅርጽም ተመሳሳይ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
ሃና ተሰማ
ምንጭ
ቢቢሲ
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት









