
አዲስ አበባ: | ጥር 18 2015 | NBC Ethiopia – የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ሚርጃና ስፖልጃሪክ ኤገር ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም መንግሥት የሰላም ስምምነቱን በቁርጠኝነት እየተገበረ መሆኑን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅትም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች በተጠናከረ መልኩ ወደ አገልግሎት እንዲጀምሩ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትንም የማስፋፋት እና የማጠናከር ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት አቶ ደመቀ፥ በግጭቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ የመግንባት እና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉን አቀፍ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኀበር ኮሚቴ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋር አካላትም እስካሁን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት እና በድርቅ ምክንያት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልፀዋል።
የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ሚርጃና ስፖልጃሪክ ኤገር በበኩላቸው ማኅበሩ በኢትዮጵያ የሚሰጠውን ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ፕሬዚዳንቷ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ሁኔታ ተስፋ ሰጭ መሆኑን የገለፁ ሲሆን፤ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ በማስፋት አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡









