ጥር 17 ቀን 2015– ሕንዳዊው ካናን አምባላም (ዶ/ር) በወለጋ ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ የሕዝብ አስተዳደር እና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ላከናወኗቸው ሥራዎች ከሕንድ መንግሥት ከፍተኛ የተባለው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

NBC Ethiopia
እንደሚታወቀው የሕንድ መንግሥት በተለያዩ አገራት ለሚኖሩ ዜጎቹ በተገኙበት አካባቢ ማኅበረሰቡን ለመለወጥ የሚሰሩትን ሥራዎች በመመልከት በየሁለት ዓመቱ ሽልማትን ይሰጣል።
ጥር 02/2015 ዓ.ም. ከሕንድ መንግሥት እጅ ፕራቫሲ ባሃራቲያ ሳማን ሽልማት (PBSA) የተባለውን ከፍተኛ ሽልማት የተረከቡት ካናን አምባላም፣ አዲስ አበባ ከሚገኘው የሕንድ ኤምባሲም የተሰጣቸውን ሽልማት በመጥቀስ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል።
የወለጋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ሐሰን የሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው “የየትኛውም አገር ዜጋ ቢሆንም በርትቶ ከሠራ እና መልካምነትን ካደረገ ሁሌ በበጎ ሽልማት ይመለሳል” ብለዋል።
ካናን አምባላም (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም በወለጋ ዞኖች እና በምዕራብ ጉጂ ዞን በገጠር የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ሕይወት ለመቀየር ባደረጉት ጥረት ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት እና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸወም ነበር።
ሚኒስቴሩ እሳቸው እና ተማሪዎቻቸው እንዲሁም ማኅበረሰቡ በመቀናጀት ያከናወኑትን ሥራ እውቅና በመስጠት ሌሎች ፕሮጀችቶችን ለመደገፍ የሚውል 25 ሺህ ብር በሽልማት መልክ ሰጥቷል።
“የተለያዩ ሽልማቶችን ከተለያዩ አካላት ተቀብለናል። አሁን ይህ በሕንድ መንግሥት የተሰጠን ግን የተለየ ነው። ሽልማቱ የበለጠ ኃላፊነት እንድንቀበል ያደርገናል” ብለዋል ዶ/ር ካናን።
ከሕንድ መንግሥት ለካናን አምባላም የተሰጠው ይህ ሽልማት ከፍተኛ የተባለ እና የተከበረ ሲሆን፣ በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ሕንዳውያን በተለያዩ ዘርፎች ለኅብረተሰብ እድገት ላከናወኑት ሥራ በየሁለት ዓመቱ የሚሰጥ ነው።
ዶ/ር ካናን “ይህንን የኅብረተሰብ ችግርን የመፍታት ሥራ ላላፉት 10 ዓመታት ስንሰራ ቆይተናል። ይህ ሽልማት ደግሞ ለዚህ የተሰጠ እውቅና ስለሆነ የበለጠ ያበረታታናል። ለሽልማቱም የሕንድን መንግሥት ማመስገን እወዳለሁ” ብለዋል።
ዶ/ር ካናን በወለጋ ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ፋክልቲ የሕዝብ አስተዳደር እና ልማት ውስጥ ከ12 ዓመት በላይ አስተምረዋል።
ከ10 ዓመታት በላይ ደግሞ ከማስተማር ጎን ለጎን የገጠሩን ማኅበረሰብ የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶች ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል።
በአነስተኛ ወጪ ድልድዮችን መገንባት፣ ምንጮችን ማጎልበት፣ የገጠር መንደሮች የኤሌትሪክ ብርሃን እንዲያገኙ ማድረግ እና የአርሶ አደሩ ማሳ ውሃ እንዲገባለት የመስኖ ሥራ ላይ ተማሪዎቻቸውን እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማሳተፍ የሚሰሯቸው ፕሮጀክቶች ናቸው።
ዶ/ር ካናን ከዚህ ቀደምም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ከሰሩላቸው የማኅበረሰብ አካላት እና ከወለጋ ዩነኒቨርስቲ ሽልማቶችን ተቀብለዋል።









