በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር አካባቢ እየተጠናከረ የመጣው የኃይል ፉክክር፣ የሶማሊያ መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያለው የዲፕሎማሲ ውጥረት፣ የግብጽ በሶማሊያ ያላት ተሳትፎና የሁቲ አማጽያን በቀይ ባህር የሚፈጽሙት ጥቃት የቀጠናውን የፖለቲካና የደህንነት ሁኔታ እየፈተኑት እንደሚገኙ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዲሁም በNBC ኢትዮጵያ የ”ዓለም አቀፍ” ፕሮግራም ተባባሪ አዘጋጅ ትዕዛዙ መሐመድ፣ በቻይና ሼንዘን በተካሄደው የእስያ-ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር (ኤፒኢሲ) ጉባኤ የአሜሪካ፣ የቻይናና የሩሲያ መሪዎች መቀራረብ ለዓለም ፖለቲካ አዲስ የዲፕሎማሲ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል። በጉባኤው የተነሱት ሃሳቦችና መግባባቶች ወደ ተግባር ከተቀየሩ ለዓለም ኢኮኖሚና ደህንነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

እንደ መምህሩ ገለፃ፣ በዓለም ኃያላን ሀገራት መካከል የሚታየው መቀራረብ በተለያዩ ቀጠናዎች ያሉ የደህንነት ስጋቶችን በራሱ ሊፈታ እንደማይችል ጠቁመው፣ በመካከለኛው ምሥራቅ በሆርሙዝና በባብ ኤል-መንደብ የባህር መተላለፊያዎች ላይ የሚታየው የመዘጋት ስጋት በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ከባድ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል አብራርተዋል። በየመን የሚንቀሳቀሱት የሁቲ አማጽያን በቀይ ባህር የሚያደርሱት ጥቃት የንግድ መስመሮችን ከማወክ ባለፈ ግጭቱ ወደ አፍሪካ ቀንድ እንዲስፋፋ ሊያደርግ እንደሚችል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
ይህ የደህንነት ስጋት ከአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ፉክክር ጋር የተቆራኘ መሆኑን ያነሱት መምህሩ፣ በተለይ ግብጽ በሶማሊያ የምታደርገው እንቅስቃሴ ከሰላም ማስከበር ተልዕኮ ባለፈ በኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካና የደህንነት ጫና ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል።
በተለይም በሱዳን የተቀጣጠለው ጦርነት የቀጠናውን መረጋጋት ከመፈተኑ ባለፈ ለግብጽ የፖለቲካ ፍጆታ ሊዉል እንደሚችል ገልፀው፣ ሱዳን ከውስጥ ቀውሷ ወጥታ ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የናይል ወንዝን በጋራ ለመጠቀም የምትችልበት ዕድል መኖሩ ካይሮን እንደሚያሳስባት አብራርተዋል።

ግብጽ በኤርትራ ያላት ተጽዕኖ የዚሁ ፖሊሲ ማሳያ እንደሆነ ያነሱት መምህሩ፣ ሀገሪቱ ከግብጽ ጋር ያላት ግንኙነት ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማት ያበረከተው አስተዋጽኦ እንደሌለ አስታዉሰው፣ ግብጽ በሰሜን በኩል ኤርትራን በመጠቀም ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር እንዳገለለች ሁሉ አሁንም በምሥራቅ በኩል ተጨማሪ የጫና ግንባር ለመክፈት እየሠራች እንደሆነ አመልክተዋል።
ከዚህ አንጻር ግብጽ ከአልሸባብ ጋር ልትሰራ እንደምትችል ተናግረው፣ ይህ ስጋት ከግብጽ የቀድሞ የቀጠናዊ ግንኙነቶች ጋር ተያይዞ የሚታይ ሲሆን፣ በሱዳን፣ በኤርትራና በሶማሊያ የሚታዩ ውጥረቶች ተደማምረው በአፍሪካ ቀንድ ላይ ተጨማሪ የደህንነት ስጋት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን አምባሳደር የማባረሩ እርምጃ በቀጠናው ያለውን የዲፕሎማሲ ውጥረት ይበልጥ እንደሚያባብሰው ተገልጿል። እስራኤል ለሶማሌላንድ ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ ሞቃዲሾ ወደ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ፉክክር መግባቷን ያነሱት መምህሩ፣ ከአቅሟ በላይ ከሆኑ ሀገራት ጋር ወደ ግጭት መግባቷ የዉጭ ግንኙነቷን ሊያወሳስበው እንደሚችል ተናግረዋል።

የዚህ ውዝግብ ሌላው ገጽታ በሶማሊያ የፌዴራል መንግሥትና በክልላዊ አስተዳደሮች መካከል ያለው የሥልጣን ክፍፍል መሆኑን መምህር ትዕዛዙ አንስተዋል። የሶማሊያ የ2012 የሽግግር ሕገ መንግሥት በፌዴራል መንግሥቱና በክልሎች መካከል የውጭ ግንኙነትና የሥልጣን ክፍፍልን እንዳስቀመጠ አስታዉሰው፣ እንደ ፑንትላንድና ጁባላንድ ያሉ ክልሎች በተወሰኑ የልማት ጉዳዮች ላይ ከውጭ ሀገራት ጋር የመሥራት ስልጣን እንዳላቸው አብራርተዋል።
ሶማሊያ የውስጥ አለመረጋጋትና የመበታተን ስጋት እየተጋረጠባት ባለበት ሁኔታ ከሌላ ሀገራት ጋር የሚፈጠሩ ግጭቶችን ማባባስ ለሀገሪቱ ተጨማሪ ችግር እንደሚያመጣ ያስገነዘቡት መምህሩ፣ በቅድሚያ የውስጥ አንድነቷን ማጠናከርና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባት ጠቁመዋል።
በ-በረከት አስረስ









