ኤንቢሲ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሚያዘጋጀው “የኤዲተሮች ጠረጴዛ” መርሃ ግብር የተገኙት የግጭት መከላከልና የሠላም ግንባታ ከፍተኛ ባለሞያ ፓስተር አዳነ ደቻሳ በሃገራችን አሁናዊ የግጭት ሂደትና በሃገር በቀል እሴቶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል::
በኢትዮጵያ ለዘመናት ተጠብቀው የቆዩ ባህላዊና ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ከዘመናዊ ፍርድ ቤቶች ይልቅ የዕለት ተዕለት ማህበራዊና ቤተሰባዊ አለመግባባቶችን በስፋት በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና ሲኖራቸው፣ ፍርድ ቤቶች ህግ እና መረጃ ላይ ተመስርተው አሸናፊና ተሸናፊን በመለየት ውሳኔ ሲሰጡ ሀገር በቀል የሽምግልና ስርአቶች ግን የተቀየሙ ወገኖችን በማስታረቅና የተበላሸውን ማህበራዊ ትስስር መልሶ በመገንባት ዘላቂ አብሮነትን ያረጋግጣሉ በማለት ገልጸዋል::
በየክልሉ የሚዲያ ኮሚኒኬሽን በመኖሩ የክልል ሚዲያዎች ባህላዊ የእርቅ ስርአቶችን ለማስተዋወቅ የጀመሯቸው በጎ ጥረቶች ስለግጭት አፈታት አልፎም ውጤታማነቱን የሚገልፅ ሲሆን፣ የሃይማኖት ሚዲያም ይህን ምሳሌ በመውሰድ ለሰላም ሥራ ጉልህ ሚና መጫወት እንደሚችል አመላክተዋል።
በሀገራችን ያሉ የባህላዊ ግጭት አፈታቶች መካከል የኦሮሞ ማኅበረሰብ የገዳ ሥርዓት በአባገዳዎች መሪነት ከባድ የደም መፋሰስን ጭምር በዕርቅ የሚፈታ ሲሆን፣ በአማራና በተለያዩ አካባቢዎች የሚሠራበት የሽምግልና ሥርዓት ደግሞ በተከበሩ ሽማግሌዎች አማካኝነት እርቅ ያወርዳል። በተጨማሪም የጋሞ ማኅበረሰብ የሸንጎ አውድ የሆነው ዱቡሻ፣ የሲዳማው አፊኒ እና የአኙዋክ ብሔረሰብ ዊርኩር ግጭቶችን ለመፍታትና ፍትሕን ለማስፈን የሚያገለግሉ ጠንካራ ማኅበረሰባዊ ተቋማት ሲሆኑ ጥንታዊ አሠራሮች የሀገሪቱን የበለጸገ ባህላዊ የሰላም ግንባታ ቅርስ ያሳያሉ።
አሁንም የሽምግልና ስርአቶቹን ህግጋትና ስነ-ምግባር በጥልቀት በመመርመር ረገድ ትልቅ ክፍተት እንዳለ በመግለጽ፣ አክለውም እነዚህ ሀገር በቀል እሴቶች ያልተማሩ ሰዎች ድርጊት ተደርገው ሳይናቁ በበቂ ዝግጅትና ሽፋን ለህብረተሰቡ ሊቀርቡ እንደሚገባና ይህም ለሰላም ግንባታው ሂደት ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን አመላክተዋል።
በሌላ በኩል በዲጂታል ዘመን በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት የሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች ለሰላም ግንባታው ስራ ትልቅ ተግዳሮት መሆናቸውን በተለይም በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ተራ አለመግባባቶችን የብሔር ወይም የሃይማኖት መልክ በመስጠት የሚሰራጩ የሀሰት ዜናዎች ሰላምን በከፍተኛ ደረጃ የሚያደፈርሱ በመሆናቸው ህብረተሰቡም ሆነ የሃይማኖት አባቶች እንዲህ ያሉ እኩይ ድርጊቶችን በጋራ ሊያወግዙና ሊገስጹ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመጨረሻም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የመንግስት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የመገናኛ ብዙሃን የተቀናጀና የተናበበ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው እና ግጭት ከመከሰቱ በፊት ቅድመ የመከላከል ስራዎችን መስራት በየቦታው ያሉ በጎ ማህበራዊ እሴቶችን ማጎልበት እና ሰላም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት ሁሉም አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል::
በ – የአብሥራ ተፈራ


















