ነገሩ እንዲህ ነው፣ የደቡብ ኬሮላይና ነዋሪ የሆነች አንዲት እንስት እድል ይቀናኝ እንደሆን ብላ ባለቤትዋን የሎተሪ ቲኬት ገዝቶ እንዲመጣ ትነግረዋለች።
ነገር ግን የሚስቱን ጥያቄ ዘንግቶ፤ እንዲገዛ የታዘዘውን የሎተሪ ቲኬቶች ሳይገዛ ይመለሳል። ባለቤትዋ ከሄደበት ተመልሶ ወደ ቤቱ ሲገባ የጠየቀችውን የሎተሪ ቲኬቶች መዘንጋቱን የተረዳችው ይህች እንስት እራሷ ለመግዛት ትወስናለች።
ስለዚህም በአቅራቢያዋ ወደሚገኝ የሎተሪ መሸጫ ሱቅ ታቀናለች። በዚያም “በሰልፉ ላይ ቆሜ ነበር ቀና ስል እነዚህን ብሩህ እና የሚያብረቀርቁ ቲኬቶች ዓይኔን ሳቡት ለዚያም ሦስት ትኬቶችን ገዛሁ።” ስትል የእድሏን መንደርደሪያ ታስታውሳለች።
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ትኬቶች እድል ያልቀናት ቢሆንም፤ ሦስተኛው የ500ሺህ ዶላር በረከት ይዞላት ወደ ቤቷ ጎራ ብሏል። ባገኘችው ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት መደሰቷን ጠቅሳ፣ የባለቤትዋ ዝንጉነት የእድሏ በር ከፋች ምክንያት እንደነበር ተናግራለች።
ዩፒአይ ዶት ኮም ይግረማችሁ ሲል አጋርቶናል።












