ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ በቻይናው ሺ ጂንፒንግ የረዥም ጊዜ ወዳጅ (ኦልድ ፍሬንድ) ሲባሉ ፤በዶናልድ ትራምፕ የጓደኛዬ ስም ተሰጥቷቸዋል፡፡ የትራምፕ ከእኔ በላይ ማን አለ፤የፑቲን ታክቲክ እና የሺ ስትራቴጂ ጉባዔ በሚልም ተንታኞች የሶስቱን ሀገራት መሪዎች ውይይት ገልጸውታል፡፡ የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ፣ጦር ፣ዲፕሎማሲ፣ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት መሪዎች አንድ መድረክ ላይ በሸን’ጀን ቻይና መገናኘታቸው ታረካዊ ሆኖ ተመዘግቧል፡፡

ሺ ጂንፒንግ፣ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን የንግግራቸው ውጤት ምንም ይሁን ፤ሶስቱ በአንድ ጠረጴዛ ላይ መገናኘታቸው ታሪካዊ ክስተት አስብሎታል ፡፡ በተናጠል እንጂ ሶስቱ ግዙፎች አንድ ላይ መክረው ፈጽሞ አያውቁም ፡፡የኤዥያ -ፓስፊክ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ጉባኤ (APEC) ደግሞ ለውይይቱ እድሉን ፈጥሯል ፡፡
የፑቲን፣ሺ እና ትራምፕ መገናኘት የ1945ን የጦርነት ጊዜ “የልታ ኮንፈረንስ ” የሚያስታውስም ነው ፡፡ ምናልባትም እንግሊዝ በቻይና፤ክሪሚያ በሸንጀን ከመተካታቸው ውጭ የዛሬ 8 አስርት ዓመታት ዓለም የነበረችበትን ነውጥ በንጻሬ የሚያሳይ ነው ፡፡ የልታ ኮንፈረንስ ከፈረንጆቹ የካቲት 4-11 /1945 ድረስ ሲካሄድ የዛኔዋ ሶቭዬት ኅብረት ጆሴፕ ስታሊን፣የአሜሪካው ፍራንክሊን ዲ ሩዝቬልት እና የዩናይትድ ኪንግደሙ ዊንስተን ቸርቺል የናዚ ጀርመንን የመጨረሻ ሽንፈት እቅድ ያወጡበት፤ጦርነቱ ሲጠናቀቅም በአውሮፓ ምን ዓይነት ስርዓት ይኑር የሚለውን በግልጽ ያዩበት አጋጣሚ ነበር ፡፡ታዲያ የየልታው ኮንፈረንስ ሞስኮ በምስራቅ አውሮፓ ጡንቻዋን እንድታበረታ እድል የፈጠረ ነው እንደሚባለው ሁሉ፤ዛሬም የፑቲንን ጡንቻ ሊያዳብርላቸው እንደሚችል ተንታኞች ያስቀመጣሉ፡፡

በዘመናዊቷ ዓለም ታሪክ የሶስቱ ኃይላት፤ የቤይጂንግ ፣ዋሽንግተንና ሞስኮ መሪዎች መገናኘት ዓለም ወደ አዲስ ምዕራፍ እያመራች መሆኑን የሚጠቁምም ያደርገዋል ፡፡ ለዚህም ነው የየልታው ኮንፈረንስ፤ በቻይና ምድር ሸንጀን ታሪክ ተደገመ እየተባለ የሚገኘው ፡፡ የየልታው ኮንፈረንስ በአንድ ግንባር የተሰለፉትን ሞኮስኮን፣ዋሽንግተንና ለንደንን ከ80 ዓመታት በፊት ያገናኘ ሲሆን ዛሬ ላይ በታሪካዊ አጋጣሚ አንድ መድረክ ላይ የተገኙት መሪዎች ግን አጅንዳቸው የየቅል እንደሆነ ይነገራል ፡፡ ሀገራቱ የተለያየ የዓለም አቀፍ ህግ አተገባበር እና ስርዓት ዓላማ ያላቸው ናቸው፡፡
ምናልባትም ሺ ጂንፒንግ እና ፑቲን በተመሳሳይ መድረክ ላይ ናቸው ማለት ይቻል ይሆናል እንጂ ያን ያህል መሪዎቹ የሀገር ውስጥ ጉዳዮቻቸውን ቸል ብለው ዓይን ለዓይን ተያይተው ይግባባሉ ማለት እንዳልሆነም ታሳቢ ይደረጋል ፡፡
ውጥንቅጡ በወጣ ዓለም ላይ ሆነው ያደርጉት ውይይት ውጤቱ እንደትላንቱ በቀላሉ የሚፈታ፤በታሰበው ልክ የሚሄድ እንደማይሆንም ይገመታል፡፡ ሶስቱም መሪዎች በተለያየ አቋም ላይ ናቸው፡፡ የደብሊን ዩንቨርሲቲ ኮሌጁ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ፕሮፌሰሩ ስኮት ሉካስ ጉባዔው የትራምፕ የበላይነት ስሜት፣የፑቲን ታክቲክ እና የሺ ጂንፒንግ ስልታዊነት ነው ማለታቸውም ይህንኑ ያሳያል፡፡ ከባለ 21 ሀገራት ዓባላቱ ኤፔክ ጉባዔ ጎን ለጎን የሦስቱ ግዙፎች ውይይት፤ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያነሳ እንጂ መፍትሄ ሰጭ ሊሆን እንደማይችል ቀድሞውንም የተገመተ ነበር ፡፡
ትራምፕ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ከተገዳዳሪዎች ጋር አለማውራታቸውን ተችተዋል ፡፡ በእርግጥም ዋሽንግተን ከሞሰኮና ቤይጂንግ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ፍጥጫ አንድም በንግዱ፤አንድም በቴክኖሎጂውና በስለላው፤አለፍ ሲልም በጦር መገዳደሩን በዲፕሎማሲው ካልተካችው መውደቂያዋን እንደማፋጠን ይቆጥሩታል ፡፡
ሪፐብሊካኑ በአትላንቲኩ እና አርክቲኩ እስከ ጥቁር ባህር ጫፍ ሩሲያን ፤በኤዥያ ፓስፊክ እና በኢንዶ ፓስፊኩ ቀጠና ቻይናን ለመገዳደርም ሆነ በአጋርነት አብሮ ለመዝለቅ ዲፕሎማሲን እንምረጥ ሳይሉ አልቀሩም ፡፡ ያም ሆኖ ትራምፕ በተገኙበት መድረክ ሁሉ አሜሪካ አንደኛ ፤በአንጻሩ ሩሲያንና ቻይናን በሁሉም ጉዳይ ከዋሽንግተን ዝቅ አድርገው ደረጃ ይሰጧቸዋል ፡፡
ትራምፕ የምድሪቱን 52 በመቶ ክፍል የሚካልለውን የኢንዶ -ፓስፊክ ዕዛቸውን ተጠቀመው ቻይናን ከበባ ውስጥ ማስገባት ውጥናቸው ብቻ አይደለም ፡፡ የጂኦፖለቲካ፣ ጂዖቴክኖሎጂ እና የጂኦፋይናንስ ወይም ኢኮኖሚ ተገዳዳሪነትንም የሙጥኝ ብለውታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የዓለምን የፖለቲካ አተነፋፈስ እያዩ የሚቆሙ ሳይሆኑ፤የአሜሪካን የውስጥ ፖለቲካ ግራ ቀኝ እያዳመጡ መጓዝንም መምረጥ ግዴታቸው ሆኗል፡፡
ቻይና እና ሩሲያ በአሁኑ ሰዓት ከወዳጅ በላይ የሚተያዩ ፤ገደብ የለሽ አጋርነት ውስጥ ያሉ ናቸው ፡፡ ሞስኮ በኪዬቭ ላይ ጦር ከቀሰቀሰችበት ጊዜ አንስቶ የሩሲያ ቁጥር አንድ የንግድ ወዳጅ ቻይና ናት ፡፡ ሺ እና ፑቲን ቀድመው ዶልተው ትራምፕን ጠብቀዋቸዋል ፡፡ ፑቲን ከሶስትዮሽ ውይይቱ በፊት የቀድሞ የበላይ ነን ባዮች በሚል ምዕራቡን ዓለም በጥቅሉ፤አውሮፓውያኑን ደግሞ እየደከሙ ያሉ ሲሉ መጥራታቸው ስትራቴጂያቸው ምን ላይ እንዳለ ጠቋሚ ያደርገዋል ፡፡

መሪዎቹ በዝግ ለ1፡30 ያህል ተወያይተዋል ፡፡ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ደግሞ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ክልከላ እንዲደረግ እና እንዲወድም ጥያቄ አቅርበዋል ፡፡ የኑክሌር ጦርነት በፍጹም አሸናፊ አይኖረውም ፤ሊኖርም አይገባም ፤ከኑክሌር ነጻ ዓለምን እንገንባ የሚል ጥሪም ቀርቧል ፡፡ ሺ ጂንፒንግ ስብሰባውን አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና ታሪካዊ ያሉት ሲሆን ለአዳዲስ ጉዳዮች በር ከፋችም ነው ብለውታል ፡፡ ሶስቱም ሀገራት የቀዝቃዛውን ዓለም ጦርነት ግንዛቤ እርግፍ አድርገው እንዲተውትም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
ከመገፋፋት አንድ ላይ በኃላፊነት መስራት ወሳኝነት እንዳለውም ፕሬዚዳንቱ አጽንዖት ሰጥተዋል ፡፡ በመከባበር ዓለምን መታደግ ይቻላል ባይ ናቸው ሺ ጂንፒንግ፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ታሪክ ሰርተናል ሲሉ ቭላድሚር ፑቲንም ሩሲያ፣ቻይናና አሜሪካ ዓለም አቀፍ ደኅንነትን ለማምጣት የጋራ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የውይይቱ ትኩረት አለመሆኑም ይፋ ሆኗል ፡፡

“ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን ጋር ለመነጋገር ወጥነው ነበር ሳይሳካላቸው ከቻይና ወጡ፤ቻይና ሩሲያ እና አሜሪካ በሶስቱ ሀገራት መካከል ያለው የኃይል ፍሰትን ለማረጋገት ቃል ገቡ፤ሀገራቱ በኑክሌር ጉዳይ ላይ መፍትሄ እንደሚያሻ ተወያዩ፤ባለድሉ ፑቲን ናቸው፤ከሶስትዮሽ ውይይቱ አትራፊው ናቸው”የኢራን ጉዳይ እና መሰል ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች የትራምፕ ሺ እና ፑቲን የ1፡30 ቆይታ ጥቅል ሀሳቦች ናቸው፡፡
በ-ቢኒያም ካሴ









