የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኮሪደር ልማት ዙሪያ በተለያዩ ስፍራዎች ተዘዋውረው ባደረጉት ምልከታና በሰጡት ማብራሪያ፤ 3ኛው ዙር የኮሪደር ልማት ከካዛንቺስ ቀጥሎ የተከናወነ ረጅሙ ኮሪደር መሆኑን ገለጹ
ልማቱ በአጠቃላይ በስድስት ሎት ተከፋፍሎ የተሰራ ሲሆን፣ በእነዚህ ሎቶች ውስጥ ወደ 90 የሚጠጉ ህንፃዎች መገንባታቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል።
ከ3ኛው ዙር የኮሪደር ልማት መስመሮች መካከል አንደኛውና ረጅሙ ከቦሌ መድኃኒዓለም እስከ እንግሊዝ ኢምባሲ ድረስ የሚዘልቀው መሆኑም ተመላክቷል።
በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ ከኢምፔሪያል ሆቴል እስከ ሻላ መናፈሻ፣ ከቺቺኒያ እስከ ቦሌ ሩዋንዳ እንዲሁም ከአደይ አበባ ስታዲየም እስከ ቦሌ መንገድ ያሉ ስፍራዎችን የሚያካትት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል።
የልማት ስራው በድምሩ 57 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፣ የመሰረተ ልማት አቅሙም በቁጥር ሲታይ ሰፊ መሆኑ ተገልጿል። በዚህም መሰረት 17 ኪ.ሜ. የመንገድ ርዝመት፣ 34 ኪ.ሜ. የእግረኛ መንገድ እና 8 ኪ.ሜ. የባለሁለት እግር ተሽከርካሪ መንገድ መካተታቸውን እንዲሁም 3 የተሽከርካሪና የእግረኛ መሻጋገሪያ ድልድዮች መገንባታቸውን አስረድተዋል።
የኮሪደር ልማቱ የመንገድና የመሸጋገሪያ ቦታዎችን ብቻ ሳይሆን የከተማዋን የመዝናኛና የስፖርት አማራጮችን በማስፋት ላይ ያተኮረ ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ በ57 ሄክታር የልማት ቦታ ውስጥ የሚገኘው መሬት በብዛት ፕላዛዎችን፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን፣ የልጆች መጫወቻዎችን እንዲሁም የእጅና የእግር ኳስ ማዝወተሪያ ቦታዎችን የያዘ መሆኑን ነው የገለፁት።
ስለ ከተማዋ ለውጥ ሲነሳ ቀዳሚ ከሚባሉት አገልግሎቶች አንዱ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) መሆኑን ጠቁመው፣ በአንድ ጊዜ 5,880 መኪናዎችን ማቆም የሚያስችሉ ቦታዎች መካተታቸውን ገልጸዋል።ከዚህ ጎን ለጎንም የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ታሪካዊና ማህበራዊ እሴቶች በማጉላት፣ ለሀገር ባለውለታዎች በከተማዋ አደባባይ ሀውልት የማቆም ስራን አካቷል። ከእነዚህም መካከል በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱትና የአፍሪካ የእግር ኳስ አባት በመባል የሚታወቁት እንዳልካቸው ተሰማን የሚያስታውስ ሀውልት መሰራቱን ከንቲባዋ በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል።
የከተማችንን ውበትና ዘመናዊነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረው የሦስተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሲመረቅ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና ታላላቅ ባለስልጣናት በደማቅ ሁኔታ ታድመውበታል።
በ -ታደለ ገበየሁ









