ባህል የአንድን ሀገር ማንነትና ታሪክ ከመግለጽ ባለፈ፣ ሕዝቦችን የሚያቀራርብና የጋራ መግባባትን የሚያጠናክር ድልድይ ነው። ሀገራት ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውንና የጥበብ ውጤቶቻቸውን ለዓለም ለማስተዋወቅ ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል የባህል ማዕከላት ዋነኞቹ ናቸው። እነዚህ ተቋማት የባህል ልውውጥን ከማበረታታት ባለፈ ለኪነ-ጥበብና ለዕውቀት ሽግግር ወሳኝ መድረኮች ሆነው ያገለግላሉ።

በኢትዮጵያ የአድዋ ጦርነት ድልን ተከትሎ በርካታ ሀገራት ያላቸውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተዋል፤ ከዚህ መካከል ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ሩሲያና እንግሊዝ የመሳሰሉ ሀገራት የባህል ማዕከላትን በማቋቋም የቋንቋ፣ የባህልና የጥበብ ልውውጥን አጠናክረዋል።
”ደቦ ስልሳ ደራሲያን” በተሰኘው የእንዳለ ጌታ መጽሐፍ ውስጥ፣ “የባህል ማዕከል ግንባታ የብሔረሰብ መንደሮችን ለማዳን” በሚል ርዕስ በሰፈረው መጣጥፍ ላይ ብርሃኑ ሰሙ እንዳብራሩት፣ እነዚህ ማዕከላት የራሳቸውን ባህል ከማስተዋወቅ ባለፈ ለኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብና ኪነ-ጥበብ እድገት የጎላ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

በሀገራችን ከሚገኙት የውጭ ባህል ማዕከላት መካከል የፈረንሳዩ አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴሲ፣ የጣሊያንና ጀርመን የባህል ማዕከላት እንዲሁም የሩሲያ የሳይንስና ባህል ማዕከል በግንባር ቀዳምነት ይጠቀሳሉ። ዋነኛ ዓላማቸውም የሀገሮቻቸውን ቋንቋና ባህል ማስተዋወቅ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የጥበብ እንቅስቃሴና የሕዝቦች ትስስር ላይም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
ለአብነት፣ መጀመሪያ ላይ ፈረንሳይኛ ቋንቋን ማስተማርን ዋና ዓላማው አድርጎ የተቋቋመው አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴሲ፤ በሂደት ተግባሩን በማስፋት ራሱን የቻለ የባህል ክፍል ማቋቋሙ የሁለቱን ሀገራት የጥበብ ትስስር ይበልጥ አጠናክሮታል።

በተጨማሪም ማዕከላቱ ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል የውጭ ሀገራት አርቲስቶችን ከኢትዮጵያውያን ጋር ማገናኘት፣ የሥራ ልምድ እንዲለዋወጡና የጋራ የጥበብ መድረኮች ላይ እንዲሰሩ ማመቻቸት ይገኙበታል። በተለይም በሥዕልና በፎቶግራፍ ዘርፍ የሃገር ውስጥ አርቲስቶች ሥራዎቻቸውን በዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች ላይ እንዲያቀርቡ እድል ይፈጥራሉ።

የተቋማቱን ሰፊ ተደራሽነት በተመለከተ በ”አዲስ ዜና” ጋዜጣ ላይ እንደሰፈረው፣ ለአብነት ያህል የጀርመን የባህል ማዕከል በየዓመቱ ከ100 በላይ መርሃ ግብሮችን የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎችም ይሳተፉባቸዋል። ፊልሞች፣ የውይይት መድረኮች፣ ቴአትሮችና ኤግዚቢሽኖች ከሚዘጋጁባቸው መርሃ ግብሮች መካከል ይጠቀሳሉ። ከዚህም ባለፈ ማዕከላቱ በሀገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይቶችን በማዘጋጀት በሕዝብ መሃል የሐሳብ ልውውጥ እንዲሁም የጋራ መፍትሔ ማፈላለጊያ መድረክን በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው።

ከዚህ ባለፈም የተለያዩ የሙዚቃ፣ የዳንስ፣ የድራማና የሰርከስ ትርዒቶችን በማቅረብ፣ የፊልም ፌስቲቫሎችን፣ ሴሚናሮችንና ወርክሾፖችን ያዘጋጃሉ።በተጨማሪም መጻሕፍትን፣ የምርምር ጽሑፎችንና ሌሎች የሕትመት ውጤቶችን በማቅረብም የዕውቀት ተደራሽነትን እያሰፉ ይገኛሉ።
በ-በረከት አስረስ










