
ብሄራዊ ጥቅም የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ ህልውና አጽንቶ የሚያቆም፥ ሉአላዊነትን የሚያስከብር አልፎም ዘላቂነትን የሚያጠነክር መሰረት ነው ተባለ::
በኢንቢሲ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን «የኤዲተሮች ጠረጴዛ» በተሰኘው የመርሐ-ግብር “የብሔራዊ ጥቅም ትርጓሜ እና ሕገ-መንግስታዊ ማዕቀፍን” በተመለከተ ሰፊ ትንታኔ ተሰጥቷል::
እንግዳ ሆነው የቀረቡትም ጋዜጠኛ ኤልያስ ተክለወልድ እና መምህር አሌክስ ብርሃኑ ለሀገር ብሎም ለዜጎች የጋራ ቋንቋ ሊሆን የሚገባው እና ብሔራዊ ጥቅምን በውል ሊመዝን የሚችለው ብቸኛው መሠረት የሀገሪቱ ሕገ-መንግስት ነው በማለት ገልጸዋል።

ይህም መሰረታዊ ጥቅም ከየትኛውም የመንግስት ወቅታቂ ፖሊሲ፣ ከግል ስሜት ወይም ከቡድን ፍላጎቶች በላይ እንደሆነም መምህር አሌክስ ገልጸዋል::
በአሁኑ ወቅት በብሄራዊ ጥቅም አተገባበር እና ትርጓሜ ላይ ከመገናኛ ብዙኃን እና ከተለያዩ ፖለቲከኞች አኳያ ሰፊ ክፍተቶችና የተሳሳቱ አመለካከቶች በብዛት እንደሚስተዋሉም አብራርተዋል።
አንዳንዶች ይህንን ጉዳይ ከወቅታዊ የመንግስት ፍላጎት ጋር ብቻ ለማያያዝ ሲጥሩ፥ ሌሎች ደግሞ ከቡድናዊ ወይም ከግል ማንነት ጋር አቆራኝተው በማሳነስ ሀገራዊ አቋሙን ሲያኮስሱት ይስተዋላል ብለዋል።
ጋዜጠኛ ኤልያስ በበኩላቸው በየትኛውም ዘመን የመንግስት ለውጦች ሊኖሩ የሚችሉ ቢሆንም፥ የሀገርን ዘላቂነት እና የህዝብን መሰረታዊ ፍላጎት አስጠብቆ ለማሻገር ሕገ-መንግስታዊ ማዕቀፉን እንደ ዋና መመዘኛ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

ብሔራዊ ጥቅም ከግለሰብና ከቡድን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ወጥቶ በሕገ-መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲቃኝ ሰፊ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር እና ተከታታይ ውይይቶችን ማድረግ ወሳኝ እና ጉልህ ሚናን እንደሚፈጥር ያስረዳሉ።
በሕገ-መንግሥት ደረጃ የሚሰጠው የብሔራዊ ጥቅም፥ መንግሥት ሥልጣኑን ተጠቅሞ የሚወስናቸው ማናቸውም የአገር ውስጥና የውጭ ፖሊሲዎች የሕዝብን ሕልውና፣ ሰላምና ብልጽግና የማይጋፉና ሕጋዊ መስመር የተከተሉ እንዲሆኑ ማድረጊያ አቅጣጫ አመልካች ነው።
በ – የአብስራ ተፈራ












