
የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግስት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ስኬታማ ለማድረግ ቅንጅታዊ ጥረት ወሳኝ መሆኑን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
በኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በግብርና ትራንስፎርሜሽን የምግብና ስነ ምግብ ዋስትና ፕሮጀክት አማካኝነት በሐመር እና በናፀማይ ወረዳዎች ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ ሁለት የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል።
ፕሮጀክቶቹ ከ5 ሺህ በላይ አርብቶ አደሮችን በንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ተመላክቷል።
በምድር ውስጥ የውሀ ማጠራቀሚያ ታንከር የተገነባላቸው ሁለቱ የአሸዋ ግድብ ፕሮጀክቶቹ እያንዳንዳቸው 24 ሚሊዮን ሊትር ንፁህ የመጠጥ ውሃ የመያዝ አቅም እንዳላቸውም ነው የተገለጸው።
ፕሮጀክቶቹ የውሃ ሥርገትና ትነትን በመከላከል የዝናብና የወንዝ ውሃን ለረጅም ጊዜ ይዞ በማቆየት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ መሆኑም በምረቃ ሥነስርአቱ ላይ ተገልጿል።
የቀድሞ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሮማን ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፕሮጀክቶቹን ሲመርቁ፣ የአሸዋ ግድብ በኬንያ ተሞክሮ ውጤታማ የሆነ በተለይ ዝናብ አጠር በሆኑ ቆላማ አካባቢዎች ተመራጭ ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጸዋል ።
ዛሬ የተመረቁት ሁለቱ የአሸዋ ግድብ ፕሮጀክቶችም የአርብቶ አደሩን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር የሚፈቱና እና ለአካባቢው ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የአርብቶ አደሩን ኑሮ በዘላቂነት ለመለወጥ የመደመር መንግሥት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ ቅንጅታዊ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ በኩል ፋውንዴሽኑ የበኩሉን አገዛ ያደርጋል ብለዋል።
ቴክኖሎጂው ውጤታማ በመሆኑም በቀጣይ በሌሎች ዝናብ አጠር አከባቢዎች ፕሮጀክቶቹን የማስፋፋት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚከናወንም አመልክተዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ የዕቀባ እርሻ፣ የአሸዋ ግድብን ጨምሮ ለአካባቢያዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በትምህርት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ነው የገለጹት።
ዛሬ የተመረቁት የአሸዋ ግድቦች በአካባቢው የሚስተዋለውን የመጠጥ የውሃ እጥረት ችግር የቀረፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሐመር ወረዳ የሻንቆ ዎልፎ ቀበሌ ነዋሪ አልጋ ሌሊ እና የበናፀማይ ወረዳ የአልቲ አርጉዴ ቀበሌ ነዋሪ ቡሩ ኃይል እንደገለፁት በአካባቢው ከፍተኛ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል።
በዚህም ውሀ ፍለጋ ርቆ ለመጓዝ እና ለውሃ ወለድ በሽታዎች ሲጋለጡ መቆየታቸውን አስታውሰው በተለይ በሴቶች ላይ ከፍተኛ የሥራ ጫና ሲፈጠር መቆየቱንም አስረድተዋል።
አሁን በአካባቢው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በመገንባቱ ችግሩን እንደተፈታላቸው ጠቁመው፣ ከብቶቻቸውንም በቅርበት ውሃ የማጠጣት ዕድል ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በፕሮጀክቶቹ የምረቃ መርሃ ግብር ላይ የፋውንዴሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬን ጨምሮ የፌደራል እና የደቡብ ኦሞ ዞን አመራሮች እንዲሁም የማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።












