በአዲስ አበባ ከተማ ተወልዳ በልጅነቷ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አሜሪካ ያቀናችው ሜላት ኪሮስ፣ ከ “አዲሱ ትውልድ” (Gen Z)ለአሜሪካ ኮንግረስ የተመረጠች የመጀመሪያዋ ሴት በመሆን ታሪክ ሰርታለች።

የ29 ዓመቷ ሜላት በኮሎራዶ ግዛት በተካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ፣ የዴሞክራት ፓርቲን ወክላ አሸንፋለች። በግዛቱ የረጅም ዓመታት የኮንግረስ አባል የነበሩትን ዲያና ዴጌትን ያሸነፈችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ፣ በምርጫው ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገበች በኋላ ማክሰኞ ዕለት በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ የኮንግረስ መቀመጫ ማግኘቷ ተዘግቧል።
እ.ኤ.አ. በ1997 የተወለደችው ሜላት፣ በዋሽንግተን ኮሌጅ የፖለቲካል ሳይንስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት በመከታተል በ2018 ተመርቃለች። በመቀጠልም በ2022 ከኖትርዳም ዩኒቨርሲቲ የሕግ ዲግሪዋን አግኝታለች።
በኋለም በኒውዮርክ ከተማ “ሲድሌይ ኦስቲን” በሚባል የሕግ ተቋም ተቀጥራ ብትሠራም፣ በ2023 ፍልስጤማውያንን የሚደግፉ ተማሪዎች ተቃውሞ ላይ የተነሳውን ክርክር በተመለከተ የጻፈችውን ደብዳቤ እንድታስተባብል ብትጠየቅም ባለመስማማቷ ከሥራዋ ተባርራለች።

በዚህ ምክንያት ሥራዋን ማጣቷ ለፖለቲካ ያላት ፍላጎት እንደጨመረ የምትናገረው ሜላት፣ የሕዝብ ድጋፍ በማግኘት ጠንካራ መሠረት በመጣል የምርጫ ዘመቻዋን ጀምራለች።
በእንቅስቃሴዋም እንደ ዴሞክራቲክ ሶሻሊስቶች ማኅበር (DSA)፣ ጀስቲስ ዴሞክራትስ፣ ሰንራይዝ ሙቭመንት ከተባሉ ድርጅቶችና እና ከታዋቂው ሴናተር በርኒ ሳንደርስ የፖለቲካ ድጋፍን አግኝታለች።
ወደ ኮሎራዶ በመመለስ በ2024 በዴሞክራቲክ ፓርቲ የኮንግረስ እጩ ለነበሩት ጆን ፓዶራ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሆና ሠርታለች።
እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2026 በተካሄደው የዴሞክራቲክ ፓርቲ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ከዴጌት ጋር ተወዳድራ አሸንፋ የፓርቲውን ዕጩነት በይፋ አግኝታለች።

በአጋማሽ ዘመን የምርጫ ዘመቻዋን በወጣቶች ተሳትፎ፣ በኑሮ ውድነት እና አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን ድጋፍ በመቃወም ላይ ያደረገችው ሜላት፣ ተፎካካሪዋን ዲያና ዴጌትን ስትተች ”በኮርፖሬት(ገደብ የሌለው የገንዘብ ድጋፍ) ላይ የተመሠረተች” ብላ ትላለች።
በመቀጠልም እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 3 ቀን 2026 በተካሄደው አጋማሽ አመት ምርጫ ድል በማድረግ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ ውስጥ የተመረጠች የጀነሬሽን የመጀመሪያዋ ሴት ሆናለች።
በተጨማሪም እንደ ሜዲኬይር ያሉ የጤና አገልግሎት ፕሮግራሞችንና የምግብ ድጋፍ መርሃ ግብሮችን የበጀት ቅነሳ ለመመለስ፣ ለሁሉም ዜጎች የሚደርስ የጤና አገልግሎት፣ የሕፃናትና የአረጋውያን እንክብካቤ ለማስፋፋት እንደምትሠራ ገልጻለች።
ምንጭ፦ CBS News
በ – የአብሥራ ተፈራ












