NBC Ethiopia
። ። ። ። ። ። ። ። ። ። ። ። ። ። ። ። ። ። ። ።
ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት በዘለቀው የሀገርነት ታሪኳ ውስጥ ስፍር ቁጥር በሌላቸው ችግሮች ፣ የውጭ ወረራዎች እና የውስጥ ፖለቲካዊ ውጣውረዶች ውስጥ አልፋለች። ከዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምዕራፎች መካከል ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም አንዱ ነው እጥፋት ነው።
በወቅቱ የኢትዮጵያ ሰማይ በከዋክብት ያጌጠ ቢመስልም፣ የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ግን በታሪክ የማይረሳ ጥቁር ሌሊትን አስተናግዷል። በሰላም እንቅልፍ ላይ በነበረውና የሀገርን ሉዓላዊነት ጠባቂ በሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፤ ሰሜን እዝ ላይ ያልጠተጠበቀና ያልታሰበ ጥቃት ተፈጸመ። ይህ ድርጊት የሰራዊቱን አባላት ብቻ ሳይሆን መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያስቆጣ ድርጊት ነበር።
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት በሰሜን ዕዝ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ተመጣጣኝ እና ኃላፊነት የተሞላበት አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ወታደራዊ ዘመቻን አወጀ። መንግሥት በወቅቱ ይፋ ባደረጋቸው መግለጫዎች መሰረት፣ የዚህ ሕግ ማስከበር ዘመቻ ሶስት ዋና ዋና እና የማይለወጡ ብሔራዊ ግቦች ነበሩት። አንደኛው እና ቀዳሚው ግብ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት የፈጸሙትን፣ የሰራዊቱን ሰብአዊ ክብር ያጎደሉትን እና የጦር መሳሪያዎችን በግፍ የዘረፉትን የህወሃት አመራሮች ለሕግ ማቅረብ ነበር።
ሁለተኛው ግብ የፌደራል መንግሥትን የበላይነት እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን መልሶ ማረጋገጥ ሲሆን፣ ሦስተኛውና ወሳኙ ግብ ደግሞ በህወሓት ታጣቂዎች ተዘርፈው የነበሩትን ከባድ የጦር መሳሪያዎች ከሕገ-ወጥ አካላት ማስመለስ ነበር።የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በከሀዲዎች ላይ ስትራቴጂካዊ ርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ። ሰራዊቱ ይህን ያደረገው ከአማራ ልዩ ኃይል ፣ሚሊሻና ከሌሎች ክልሎችም ጋር በመቀናጀት ከምዕራብ እና ከደቡብ ትግራይ አቅጣጫዎች ፈጣን የህግ ማስከበር ስራውን በብቃት ተወጣ።
ይህ ፈጣን የመከላከል እርምጃ በወቅቱ የነበረውን የጠላትን እኩይ ተግባር ያከሸፈ፣ የሰራዊቱን ሞራል የጠገነ እርምጃ ነበር። ዘመቻው በተጀመረባቸው የመጀመሪያ ሳምንታት ውስጥ መከላከያ ሰራዊቱ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ ነበረበት። ይሁን እንጂ የሰራዊቱ የውጊያ ስልት፣ ብልሃትና ጽናት ፈተናዎቹን በአጭር ጊዜ ወደ ድል እንዲሻገሩ አስችሏቸዋል።
የወታደራዊ እርምጃው ፍጥነት እና ውጤታማነት በመከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት በፈፀመው ህገ ወጡ ህወሃት ዘንድ እጅግ አስደንገጭ ነበር። ዘመቻው መሬት ላይ ተግባራዊ ሆኖ ከተጀመረ ከሶስት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ፣ የመከላከያ ሰራዊት የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ።
የፌደራል መንግሥቱ የትግራይን ክልል ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠርና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ማስፈኑ ያረጋገጠበት ፣ የዘመቻው አንዱ የድል ከፍታ ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል። የህግ ማስከበር ዘመቻው የመጀመሪያው ምዕራፍ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ ትርጉም ነበረው። የፌደራል መንግሥቱ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት የማስጠበቅ ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነቱን በተግባር ያሳየበት ነበር። ህዝቡም የመከላከያ ሰራዊቱ ያሳየውን መስዋዕትነት በመገንዘብ ለሀገር አንድነት የነበረውን አቋም ያጠናከረበት ወቅት ነበር።
እራሳቸውን ሰውተው የሀገርን ሕልውና ከከፍተኛ አደጋ የታደጉትን የመከላከያ ሰራዊት መዘከር ታሪካዊ ግዴታችን ነው።
ዘላለማዊ ክብር በጥቅምት 24 ጀግኖች
በ- ታደለ ገበየሁ
። ። ።
ማስፈንጠሪያውን (ሊንኩን) በመጫን NBC ኢትዮጵያን ይጎብኙ ይወዳጁ
https://linktr.ee/NBCEthiopiaTV
#NBCEthiopia
#ሆኖ_መገኘት
#Ethiopia











