
በሰሜን አፍሪካና በቀይ ባህር ቀጠና እየተለዋወጠ ያለው የፖለቲካ አሰላለፍ በግብፅ የውጭ ግንኙነት ላይ አዳዲስ ተግዳሮቶችን እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ። በተለይም ቱርክ ከሊቢያ የምስራቅ ክፍል ጋር እየተቀራረበች መምጣቷ በቀጠናው የግብፅን ተፅዕኖ ሊያዳክም እንደሚችል ተነግሯል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ትዕዛዙ መሐመድ ሲያብራሩ፣ የግብፅ የውጭ ፖሊሲና በተለያዩ ቀጠናዎች ላይ የምታራምደው አቋም የዲፕሎማሲ ተግዳሮቶችን እያበዛባት መሆኑን ገልጸዋል።

በሊቢያ በቀድሞው ግጭት ወቅት ቱርክ የምዕራቡን ፣ ግብፅ ደግሞ የምስራቁን ክፍል ሃይሎች ትደግፍ ነበር ያሉት ትዕዛዙ ፣አሁን ግን በምስራቅ ሊቢያ ያሉ ኃይሎች ከቱርክ ጋር እየተቀራረቡ መምጣታቸው የቀድሞውን የኃይል አሰላለፍ እየቀየረው ነው። ይህም የግብፅን በሊቢያ ያለ ተፅዕኖ ሊቀንስ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ካይሮ በቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ ላይ “ጉዳዩ የሚመለከተው የባህር ዳርቻ ሃገራትን ብቻ ነው” በሚል ኢትዮጵያን ለማግለል የምትሞክር ቢሆንም፤ በሜዲትረኒያን ባህር ላይ ግን የባህሩ ዳርቻ የሆኑት ቱርክና ሊቢያ ያደረጉትን የወሰን ማካለል “ህገ-ወጥ ነው” በማለት እንደምትቃወም የያዘችውን የተቃርኖ አካሄድ መምህሩ ጠቁመዋል። ይህ “በአንድ ራስ ሁለት ምላስ” የመሆን አካሄድ የግብፅን ፖለቲከኞች ስግብግብነት የሚያሳይ መሆኑን አስታውሰው፤ ግብፅ “ሜዲትረኒያን ባህር የኔ ብቻ ነው” በሚል የምታሳየው አቋም ስህተት መሆኑንም ተናግረዋል።
ቱርክ ከሞቃዲሾ ጋር ያላትን ግንኙነት በመጠቀም የግብፅን በሶማሊያ ያላትን ሚና መገደብ ከቻለች፣ ይህ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ እፎይታ ሊፈጥር እንደሚችልም መምህር ትዕዛዙ አብራርተዋል።
በቀይ ባህርና ባብ ኤል መንደብ ያለው የደህንነት ችግርም በዓለም ንግድ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በተለይም የየመኑ ሁቲዎች ጥቃት የመርከቦችን የኢንሹራንስና የማጓጓዣ ወጪ እንዲጨምር ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸዋል። በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ያላትን የወታደራዊ ልምድና የተቋማት አቅም በመጠቀም በቀጠናው የደህንነት ጥረቶች ውስጥ የበለጠ ሚና መጫወት እንደምትችልም ተናግረዋል።
የቀጠናውን አሁናዊ ሁኔታ በNBC ዓለም አቀፍ ያብራሩት የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ በተጨማሪም ሌሎች ዓለማቀፋዊ ጉዳዮችን ዳስሰዋል።
ከስር የተቀመጠውን ሊንክ በመጫን እንዲያዳምጡ እንጋብዛለን።
https://youtu.be/lJFVq_Jf9_o?si=g7OQelHxYSpk4aDQ












