
ሜጀር ጀነራል ገብረ አድሃና (ገብረ ዲላ)
በህወሃት ጠብ አጫሪነት በተቀሰቀሰው ጦርነት ወቅት የTDF ተዋጊዎች በፋኖ ጥቃት ሲደርስባቸው ነበር ሲሉ ሜጀር ጀነራል ገብረ አድሃና (ገብረ ዲላ) በኤንቢሲ ኢትዮጵያ የግዜ ግስ ፕሮግራም ላይ በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
የጦርነቱን አስከፊነት የገለፁት ጀነራሉ፣ በውጊያው ወቅት ወደፊት ዘልቆ በሚገባው የTDF ሰራዊት ላይ ጽንፈኛው ፋኖ ያልተጠበቀ ጥቃት ያደርስባቸው ነበር ብለዋል፡፡ ጀነራሉ አክለውም፣ በዚህም ምክንያት በርካታ የTDF ተዋጊዎች ከኋላ በሚከፈትባቸው ድብቅ ጥቃት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ጥቃት አድራሾቹም መሳሪያዎቹን በመዝረፍና በመውሰድ ለዳግም ጦርነት ይጠቀሙበታል፡፡ ይህን አደገኛ ድርጊትም ከውጊያ ደንብ ውጭ የሆነ ሲሉ ኮንነውታል።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀውና በፕሪቶሪያ ስምምነት በተቋጨው የሰሜኑ ጦርነት ወቅትም በህዝቡና በንብረታቸው አጠቃላይ የደረሰው ጉዳት ሲታሰብ 94 ፐርሰንቱን ያደረሱት ፋኖና ሻዕቢያ መሆናቸው በጥናት መረጋገጡን ሜጀር ጀነራል ገብረ አድሃና አስታውሰዋል ።

ሜጀር ጀነራሉ በሰጡት ማብራሪያ፣ በጦርነቱ ወቅት በህዝቡ ላይ የተፈፀሙት ግፍና በደሎች ፣ የደረሱ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶችን አስመልክቶ በተካሄዱት ዝርዝር ጥናቶች ከፍተኛውን ጉዳት ያደረሱት ሁለቱ የጥፋት ኃይሎች መሆናቸውን ነው የጠቆሙት ።
በጦርነቱ ምክንያት የትግራይ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ለከፍተኛ እንግልትና ጉዳት መዳረጉን
ገልፀው፣ የደረሱት ጥፋቶችና ወንጀሎች በመረጃ እንደሚገኙና ለወደፊትም ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ መሆናቸውን አስረድተዋል ።
ሜጀር ጀነራሉ እንደሚሉት፣ በሰሜን የሃገሪቱ ክፍል ሲካሄድ በነበረው ግጭት ወቅት ለህገወጡ የህወሃት ቡድን ከውጭ ኃይሎችም ጭምር የተለያዩ ድጋፎች ይደረጉ እንደነበር ተናግረዋል።
ድጋፋቸውን ከሚያደርጉት መካከል ግብፅ፣ ኤርትራ እና ሱዱን ተጠቃሽ ናቸው ያሉት ጀነራሉ፣ የእነዚህ ባእዳን እና ወኪሎቻቸው መቀመጫ ሱዳን ነበረች ብለዋል ።

ከውስጥም ሆነ ከውጭ የጥፋት ኃይሎች ጋር የሚደረግ ማንኛውም ጥምረትና ትብብር ሀገራችንን ለከፋ ቀውስ ይዳርጋል ያሉት ጀነራሉ፣ በሰሜኑ ክፍል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ከህግ የወጣ ከመሆኑም በላይ
የበርካታ ወጣቶችን ህይወት የቀጠፈና ህብረተሰቡን ለስደትና ለከፋ ርሃብ የዳረገ ነው ብለዋል፡፡
ሜጀር ጄነራሉ በነበራቸው ቆይታ በርካታ ወቅታዊ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን የፌዴራል መንግስት ይሄንን የጀመረውን ሰላም የማስከብር እና የክልሉን መሰረተ ልማት ወደ ቀደሞ አገልግሎቱ እንዲመለስ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በ ታደለ ገበየሁ












