
ለአሰርት ዓመታት ከገዛ ቀዬው፣ ከባህር በሩና ከማንነቱ ተነጥሎ በባዕድ ምድር መጠለያዎች ውስጥ የሚማቅቀው የቀይ ባህር አፋሮች ህዝብ፣ ዛሬ በታሪኩ ውስጥ አዲስና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ከNBC ኢትዮጵያ “ጊዜ ግስ” ፕሮገራም ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀይ ባህር አፋሮች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፍ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ አቶ ነስረዲን አሊ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የሚገኝበት ሁኔታ እጅግ አጣዳፊና አፋጣኝ ምላሽ የሚሻ ነው ብለዋል። “የቀይ ባህር አፋር ህዝቦች ላለፉት 36 ዓመታት በስቃይ ውስጥ ቆይቷል” የሚሉት አቶ ነስረዲን፤ ህዝቡ እንዲዳከም፣ ከሀገሩና ከጂኦግራፊያዊ ትስስሩ ተገልሎና የባህር በሩ ባለቤት እንዳይሆን ስልታዊ ጫናዎች ሲደረጉበት መቆየቱን በቁጭት ያስረዳሉ።
ይህንን ግፍ ለመቀልበስ ህዝቡ ላለፉት 28 ዓመታት በጽናት ሲታገል የቆየ ቢሆንም ፣ አሁን ላይ መብቱን ለማስከበርና በትግሉ ውስጥ የድርሻውን ለመወጣት ቆርጦ መነሳቱን ይገልጻሉ።
ሻዕቢያ በቀይ ባህር አፋሮች ላይ ስለሚፈጽመው የማፈናቀል ሴራ አቶ ነስረዲን ሲያስረዱ ፤ የኢሳያስ መንግስት የሚፈልገው “ባህሩን፣ መሬቱንና ሀብቱን ብቻ እንጂ ለህዝቡ ምንም ደንታ የለውም” ይላሉ።
አያይዘውም ምንም እንኳን ህዝቡ በኢትዮጵያና በጂቡቲ ከሚገኙ የአፋር ወንድሞቹ ጋር እንዳይገናኝና ወንድማዊ ትስስሩን እንዳያጠናክር ሆን ተብሎ ግንብ ቢሰራበትም ፣ ዛሬ ግን ከሩብ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ተሰዶ ከወንድሙ የአፋር ህዝብ ጋር ተቀላቅሏል ነው ያሉት።
ዛሬ የተካሄደው ኮንፈረንስ ህዝቡ ለነጻነቱ ያለውን የትግል መንፈስ ያደሰበትና ከድርጅቱ ጎን በቁርጠኝነት ለመቆም ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን ሌላኛው ስራ አስፈፃሚ አቶ አሊ አህመድ ተናግረዋል።
የቀይ ባህር አፋር ህዝቦች የገዛ ሀብታቸውን ጥለው ቢሰደዱም፣ አሁን ላይ እስከ ምፅዋ ድረስ የነበረውን የታሪካዊ ባህር በር ባለቤትነታቸውን ለማስመለስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆናቸውን አመራሮቹ ይናገራሉ።
ቀደም ሲል በባህር ዳርቻው ላይ ስኬታማ ህይወት የነበረው ህዝብ ፣ ዛሬ የሚበላውን አጥቶ ተሰዷል ። ይሁን እንጂ አሁን ባሉበት የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሚያገኙት እንክብካቤና ሰብአዊ አያያዝ በኤርትራ ከነበሩበት የባርነትና የመከራ ህይወት በብዙ እጥፍ የተሻለ መሆኑን ይገልጻሉ።
ለቀይ ባህር አፋር ህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና የአምባገነኑን ስርዓት የመገርሰስ ትግል አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
አመራሮቹ “ጊዜ ግስ” ላይ በነበራቸው ቆይታ በርካታ ቀጠናዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮችን በስፋት ዳስሰዋል።
በ-በረከት አስረስ












