NBC Ethiopia
በኤንቢሲ ኢትዮጲያ “አጀንዳ” ፕሮግራም ቆይታ የነበራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ህወሃትና ሻዕቢያ ዋና አላማቸው የአካባቢውን ሰላም ማወክ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ። በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋሉ አብዛኞቹ ግጭቶች ከስልጣንና ከሀብት ጋር የተቆራኙ እንደሆኑ አንስተዋል ።
ህወሃት በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግድ ቡድን ነው ያሉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ምክትል መሪ አቶ ንጋቱ ወልዱ፣ አክለውም ለህዝቡ የተቋቋመ ድርጅት ቢሆን ኖሮ መሰረተልማቶችን አያጠፋም ነበር ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ራሄል ባፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ህወሃት ለሚፈልገው ነገር ጦርነትን እንደአማራጭ መውሰዱ እራሱንና ንፁሃን ዜጎችን አደጋ ላይ እንዲጥል አድርጎታል ።

የወደብ ባለቤትነትን በተመለከተ አመራሮቹ በሰጡት አስተያየት፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል። ይህም ሰጥቶ በመቀበልና በሰላማዊ መንገድ ሊሆን እንደሚገባ ነው የገለፁት ።
አመራሮቹ በነበራቸው ቆይታ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።
በ – ታደለ ገበየሁ












