
በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ጀማል በከር በዱባይ አርትስ ክለብ በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ ተሳትፈዋል። “ንግድ፣ ኢነርጂ እና ተለዋዋጭ ቀጠናዊ ሁኔታ” በሚል መሪ ሀሳብ በተደረገው መድረክ ላይ ባደረጉት ገለጻ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የወደብ አማራጭ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት መሰረቱ የኢኮኖሚ ጥንካሬን ማረጋገጥ፣ ቀጣናዊ ውህደትን መፍጠር እና የረጅም ጊዜ መረጋጋትን ማስፈን መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፍላጎት ከውጥረት ይልቅ በትብብር መንፈስ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ክቡር አምባሳደሩ ፍፁም የጠብ አጫሪነት ወይም የተስፋፊነት ባህሪ የሌለው መሆኑን አብራርተዋል።
በገለጻቸውም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች የህልውና ጉዳይ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የመጀመሪያው ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ የባህር በር አልባ አገር አለመሆኗን ጠቅሰው የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ ስልጣኔና ብልጽግና ሁልጊዜም ከባህር በር ተደራሽነት ጋር በቀጥታ የተቆራኘ መሆኑ አስምረውበታል፡፡
በሁለተኛነት ከደህንነት አንጻር በቀይ ባህር ቀጠና ሽብርተኛነት እና የባህር ውንብድና በተደጋጋሚ አደጋ የደቀኑበት በመሆኑ ለኢትዮጵያ ደህንነት ቀጥተኛ ብሔራዊ ስጋት ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለህልውና እና ለቀጠናውም መረጋጋ በዚህ ዘርፍ የራሷን ድርሻ ለመወጣት የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ጠቅሰዋል፡፡
በሦስተኛነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን ያነሱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ135 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትና ግዙፍ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስ በመሆኑ አገሪቱን የጂኦግራፊ እስረኛ መሆን የማትችልበት ደረጃ ላይ መድረሷን አሰምረዋል፡፡ በአራተኛነት ያነሱት በኢትዮጰያ የውጭ ጉዳይ ፖለሲ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በአፍሪካ ቀንድ በጋራ ብልጽግና ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ ውህደትን ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡
በመቀጠልም ክቡር አምባሰደር ኢትዮጵያ ህጋዊ ጥቅሟን ለማስከበር የምትፈልገው ገንቢ በሆነ ዲፕሎማሲ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ በቀጣናዊ የመሰረተ-ልማት ትስስር
እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን ረገድ በሚኖራት ቀጣይነት ያለው ሚና መሆኑን አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት ከመካከለኛው ምስራቅ የባህረ ሰላጤው እና በአፍሪካ ቀንድ መካከል ያለው የፖለቲካ ትስስር እየጠነከረ በመምጣቱ፣ አግላይ የሆኑ የባህር አስተዳደር ስምምነቶች በቀጣናው ላይ አለመረጋጋትን ሊፈጥሩ እንደሚችሉና አካታች አሰራር ግን ቀይ ባህርን የጋራ ብልጽግና እና መረጋጋት የሚሰፍንበት ኮሪደር እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከአጎራባች ሀገራት እና ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር በቅርበት ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነት አምባሳደሩ በድጋሚ ያአረጋግጠዋል፡፡
በዱባይ በተካሄደው በዚህ የፓናል ውይይት ላይ ምሁራን፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና የንግድ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።












