
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል።
የዘንድሮው መሪ ሀሳብ በአፍሪካ የውሃ ደህንነትና ንጽህና አጠባበቅ ላይ ትኩረቱን አድርጓል። “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” የመሪዎች ጉባኤ መሪ ሀሳብ ነው።
ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተረጋገጠ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓት ዘላቂ ልማት፣ አካታች እድገት፣ ጤናማ ማህበረሰብና ጠንካራ ስነ ምህዳር መገንባት፣ የተፈጥሮ ሀብት ዘላቂ አጠቃቀምና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ከአጀንዳ 2063 ግቦች ጋር የተሳሰረ መሆኑ ተገልጿል።
የመሪዎች ጉባኤው በመሪ ሀሳቡ በጥልቀት በመምከር የተለያዩ የውሳኔ ሀሳቦች ያስተላልፋል ተብሎም ይጠበቃል።
ከመሪዎቹ ጉባኤ አስቀድሞ 48ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ የካቲት 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች፣ የሕብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የተሳተፉበት 51ኛው የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ኮሚቴ ተወካዮች (PRC) ስብሰባ ከጥር 4 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።
ስብሰባው የካቲት 4 እና 5 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ እንዲሁም የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚከናወነው 39ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይ መክሯል።
ኮሚቴው በ2026 የአፍሪካ ህብረት መሪ ሀሳብ ላይ ምክረ ሀሳቦችን አቅርቧል። የኮሚቴው መደበኛ ስብሰባ ለዋናው ጉባኤ እንደ ይፋዊ የዝግጅት ስብሰባ የሚያገለግል ነው።
ከአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ማግስት ሌላኛው በኢትዮጵያ የሚካሄደው ዘጠነኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ነው።
የቢዝነስ ፎረሙ የካቲት 9 እና 10 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሴኤ) ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሁነቱን አዘጋጅተውታል።
“የአፍሪካን መጻኢ ጊዜ በፋይናንስ መደገፍ፤ ስራ እና ኢኖቬሽን ለዘላቂ ትራንስፎርሜሽን” የፎረሙ መሪ ሀሳብ ነው።
የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በአፍሪካ የልማት እና የኢኮኖሚ እድገት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄድ ከፍተኛ አህጉራዊ የምክክር መድረክ መሆኑን የኢሲኤ መረጃ ያመለክታል።
በፎረሙ ላይ አጋርነትና የኢንቨስትመንት መጠንን ማሳደግ በተለይም የመንግስት እና የግል የተቀናጀ የፋይናንስ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይወያያል።
የወጣቶችን የኢኖቬሽን ስራ ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር የሚያስተሳስር የአፍሪካ የወጣቶች አይበገሬነትና ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ ይፋ ይሆናል።
በኢሲኤ የበለጸገውና የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ ቃል ኪዳኖችን ትግበራ የሚከታታልና የሚቆጣጠር ስርዓትም በፎረሙ ይፋ ሆኖ ወደ ትግበራ ይገባል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሁነት ላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የምክክር መድረኮችና የባለሙያዎች ውይይቶች ይደረጋሉ።
አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና የፈጣራ ባለሙያዎችን ከባለሀብቶች እና ፋይናንስ አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኝ አውደ ርዕይም ይካሄዳል።
ሁነቶቹ ቃል ኪዳኖችን ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች ለመቀየር አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ተመላክቷል።
ከአህጉራዊ ሁነቶቹ ባሻገር የባለብዙ ወገን መድረክ የሆነው የአፍሪካ እና ጣልያን ጉባኤ የካቲት 6 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤ ካለፈው ታሪካዊ ግንኙነቶች ፣ እያደገ ከመጣው የኢኮኖሚ ትብብር እና የጋራ ፈተናዎችን የመፍታት ቁርጠኝነት አኳያ በአፍሪካ
እና በጣልያን መካከል አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነ ታምኖበታል።
ኢትዮጵያ ሁነቶቹን ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።
ምንጭ፡ ኢዜአ












