46ኛው የጉሚ በለል ውይይት መድረክ “የህዳሴ ግድብ ድል ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን” በሚል መሪ ሀሳብ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ትልቅ መሰረት የጣለ የአንድነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል። የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያን በአለም መድረክ ከፍ ያደረገ ትልቅ ድል መሆኑን በመግለጽ ይህም የተቻለው በትውልድ ውድ መስዋዕት ነው ብለዋል።
የመብራት ኃይል አቅርቦት ከኢትዮጵያ አልፎ ወደ ጎረቤት አገሮች መድረሱን በመጥቀስ ግድቡ በአፍሪካ ቀንድ የኢንዱስትሪ አብዮትን የሚያስጀምር ፣ ወንድማማችነትን የሚገነባ እና ኢኮኖሚያዊ የጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እንጂ ሥጋት አለመሆኑን አንስተዋል።
የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሀይሉ አዱኛ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ከፍታ መሰረት ከመሆኑም በላይ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዲጀመሩ በር የከፈተ እና የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ኃይል ከፍ ያደረገ ነው ብለዋል።
በ-የአብስራ ብርሃኑ












