አሜሪካ በቬንዙዌላ ባህር ዳርቻ አቅራቢያ ስትንቀሳቀስ በነበረች ጀልባ ላይ ጥቃት ሰንዝራ የ6 ሰዎች ህይወት አለፈ።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ሚዲያቸው ላይ ባጋሩት ጽሁፍ ጀልባዋ’ “የአደንዛዥ ዕጽ አሸባሪዎች” ሀብት ናት ብለዋል። አደንዛዥ ዕፅን ልታዘዋውር ነበር በሚል ለጥቃቱ ምክንያት ብለው አቅርበዋል ሪፐብሊካኑ።
ከመስከረም አንስቶ አደንዛዥ ዕፅ ያዘዋውራሉ በሚል በፔንታጎን የተመቱ መርከቦች ቁጥር አምስት ደርሷል። በዚህም ቢያንስ 27 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በዓለም አቀፉ የውሃ አካል ላይ የሚፈጸም ጥቃት የህግ ጥሰት ነው በሚልም ዋሽንግተን ትከሰሳለች።
አሜሪካ ስለጀልባዎቹም ሆነ ስለጥቃቱ ሰለባዎች ዝርዝር መረጃዎችን አቅርባ እንደማታውቅም የቢቢሲ ዘገባ ይጠቁማል። አሜሪካ የምትፈጽመውን ጥቃት ከህግ አዋቂዎች በተጨማሪ ኮሎምቢያና ቬንዙዌላ በተደጋጋሚ ይቃወማሉ።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አደንዛዥ ዕጽ ይዛ ስትንቀሳቀስ የነበረችውን መርከብ መተናል የሚል ሀሳብ ከመስጠታቸውም ባሻገር ጥቃቱ በሚሳኤል ጭምር መፈጸሙ ተወስቷል። የየትኛው አገር ዜጋና ምን ዓይነት ዕጽ በጀልባዋ ውስጥ እንደነበር ግልጽ ያላደረጉት ትራምፕ አንድም የአሜሪካ ወታደር አልተጎዳም ሲሉ አረጋግጠዋል።
ዘገባው የቢቢሲ ነው
በ-ቢኒያም ካሴ












